ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Sunday, December 23, 2012

ለታህሣሥ ገብርኤል ንግሥ ወደ ሎዛን ጉዞ

ማሰታወቂያ
በሰዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የደብረ ገነት ቅድሰት ማርያም    ቤተ ክርስቲያን  የፊታችን  ዕሑድ ሕዳር  21 ቀን (30.12.2012) በሎዛን ደብረ  ይል ቅዱስ ገብርኤል  በስርዓተ ንግስ የሚከበረውን  ታላቁን የታሕሣሥ ገብርኤል በዐል ምክንያት በማድረግ ከዙሪክ የሚነሳ አውቶቡስ ለምዕመናን አዘጋጅቷል፡፡ ያልተያዙ ጥቂት ወንበሮች ስላሉ በክብረ በዓሉ ላይ በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ መሆን የምትሹ ከስር በተዘረዘሩት የስልክ ቁጥሮች በመደወል መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን በትሕትና እናስታውቃለን፡፡
ከመንፈሳዊ ሠላምታ ጋር    
                       (078) 608 85 03 \  (076) 493 96 98 \ (076) 248 88 01 
                                              
በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም   ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ የመንፈሳዊ ጉዞና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት

Thursday, December 20, 2012

አሁድ ሕዳር 14 ቀን (23.12.12) ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም   / ኦፕፊኮን እንደተለመደው መንፈሳዊ አገልግሎተ (ኪዳን) የሚኖር መሆኑን በትሕትና  እንገልጸለን፡፡

Friday, November 23, 2012

ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ

ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ



ልዩ የወንጌል አገልግሎት መርሐ ግብር በስዊትዘርላድ የኢትዮጵያ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

ተጋባዥ መምህር                                                                                           ዘማሪ

መ/ር ዘበነ ለማ /USA                                                                                ጥላሁን አብሽር


 



ጉባኤው የሚደረግባቸው ከተሞችና አድራሻ


1ኛ/ ቅዳሜ 24 ኖቬምበር 2012 በዙሪክ ከተማ ከ1500 ሰዓት ጀምሮ

Wasserkirche Limmatquai 31, 8001 Zurich

በትራም (Teram) 4 ከHauptbahnof ወደ Belview አቅጣጫ

4ኛው ማቆሚያ ላይ መውረድ ነው፡፡




2ኛ እሁድ 25 ኖቬምበር 2012 በLausanne ከተማ

ከቅዳሴ ስነሰረዓት በኃላ Villamot 13,1005 Lausanne

Bus 1 መነሻ ከባቡር ጣቢያ ወደ Blechertte አቅጣጫ

መውረጃ ጣቢያ Georgette 2ተኛው ፌርማታ በተለመደው ቤተክርሰቲያን



3ኛ/ እሁድ 25 ኖቬምበር 2012 ጄኔቫ ከ1700 ሰዓት ጀምሮ በWCC አዳራሽ

150 route de Ferney 1211 Geneva 2 በBus 5 ከCornavin ወደ

Airport አቅጣጫ መውረጃ ፌርማታ Crêts-de-Morillon



 

Sunday, October 14, 2012

በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን -ቅዳሴ እሑድ ጥቅምት 4 ቀን (October 14,2012)!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን::

የጥቅምት ወር ቅዳሴ እሑድ ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. (14.10.2012) መሆኑን እየገለጽን መረጃው ለሌላቸው ወገኖች ሁሉ አሰምታችሁ በተለመደው ሰዓት ( ክጧቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ) እንድትገኙ ቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ጥሪዋን ታቀርባለች::

የእመቤታችን ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን:: ቸር ያገናኘን:: አሜን!

Tuesday, October 2, 2012

የደመራ በዓል አከባባር በደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ዙረክ አከባበር በምስል ሲገለጽ

የዘንድሮው የመስቀል በዓል በስዊዘርላንድ የተከበረው ዕሁድ መስከረም 20 ቀን (30.9.2012) ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ሲከበረ እንደቆየው ሁሉ በዙሪክ/ኦፕፊኮን የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው::ቁጥራቸው እጅግ ከፍ ያለ ምዕመናን ከጠቅላላው ስዊዘርላንድና አጎራባች አገሮች ተገኝተው በፍቅርና በሰላም ያከበሩት ይኽው የደመራ ሥነ-ሥርዓት የመስቀልን ታሪክና ለምን እንደምናከብር በሰንበት ትምሕርት ቤት ዘማርያን በድራማ መልክ የትምሕርታዊ መልዕክት የታጀበ ስለነበር ለደመራው በዓል ልዩ ውበትና ድምቀት ሰጥቶታል::


All photos by Tesfu Woldeselassie








Monday, September 24, 2012

መምሕር ዘበነ ለማ : ዘማሪ ምንዳየ ብርሃኑና ደመራ በደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም (Glattbrugg /Opfikon), Zürich

በሰመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን::

ዕሑድ መስከረም 20 ቀን 2005 ዓ.ም.(30.09.2012)በደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኦፕፊኮን/ ዙሪክ ከጧቱ አንድ ሰዓት በቅዳሴ ከሚጀምረው መርሃ ግብር ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል - በታዋቂው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መምሕር ዘበነ ለማ የወንጌል ትምሕርት ተዋዝቶ ከኢትዮጵያ በሚመጣው ዘማሪ ዲያቆን ምንዳዬ ብርሃኑና በዙሪኩ ዘማሪ ጥላሁን አብሽር ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ደምቆ እስከ ደመራው ያደርሰናል:: ደመራው በተለመደው ቦታና ተጋባዥ እንግዶችም በሚገኙበት ኦፕፊኮን / Zunstrasse , 8152 Glattbrugg በታላቅ ሥነ-ሥርዓት እናከብራለን::

የምስራቹን ላልሰሙ ወገኖች አሰምተን በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን የድብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጥሪ ታቀርባለች::


 

Monday, August 13, 2012

የፍልሰታ ቅዳሴ በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እሑድ ነሐሴ 13 ቀን (19.08.2012)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን::

እሑድ ነሓሴ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. /19.08.2012 በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኦፕፊኮን ከጧቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ቅዳሴ ፣ በያሬዳዊ ዜማ የፍልሰታን ወቅት በሚመለከት ስብከተ ወንጌልና ተዋሕዷዊ መንፈሳዊ መዝሙሮች የሚቀርቡበት መርሃ ግብር መኖሩን እናበስራለን:: ላልሰሙ ምዕመናን አሰምታችሁ የበረከቱ ተሳታፊዎች ትሆኑ ዘንድ የሰበካ ጉባኤው በትሕትና ያሳስባል::

አድራሻው እንደተለመደው:-
Wallisellerstr.20
8152 Opfikon ነው::

Tuesday, May 8, 2012

"ሁሉም በልተው ጠገቡ:የተረፈውም ቁርስራሽ አስራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሱ::" ማቴዎስ 14:20






የግንቦት ልደታ ንግስ በጨረፍታ

የግንቦት ልደታ አከባበር - ከምስል ማሕደራችን

ዕሑድ ሚያዝያ 28 ቀን በዙሪክ/ኦፕፊኮን የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተከናወነውን የንግሥ ሥነ-ሥርዓትና በስተመጨረሻም "አድባር" በቤተ ክርስቲያኑ መናፈሻ ቦታ ላይ እንዴት እንደተከበረ በመጠኑም ቢሆን አመላካች የሆኑ ምስሎች እዚህ ላይ ተለጥፈዋል::




Monday, May 7, 2012

የልደታ በዓል እጅግ ደማቅ በሆነ ሥነ-ሥርዓት ተከበረ!

የእመቤታችን የድንግል ማርያም የልደት በዓል (ግንቦት ልደታ) እሁድ  ሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በዙሪክ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀትና ንግሥ ተከበረ:: ክተለያዩ የስዊስ ካንቶኖችና አጎራባች አገሮች በተሰበሰቡ     ምእመናን በተዋሕዷዊ መዝሙሮችና ያሬዳዊ ወረቦች ያማረውን አከባበር  የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በዚህ ገጽ ላይ ይቀርባል::
"ከሺ ቃላት አንድ ምስል በይበልጥ ይገልጻል " ነውና  ምስሎችን ይመልከቱ::
(ፎቶዎች በተስፉ ወልደ ሥላሴ)





Thursday, May 3, 2012

የግንቦት ልደታ የንግሥ ሥነ-ሥርዓት በኦፕፊኮን ደብረ ገነት ቅ.ማርያም ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል!

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

በዙሪክ/ኦፕፊኮን (ስዊዘርላንድ)የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዘንድሮውን የግንቦት ልደታን የምታከብረው ዕሑድ ሚያዝያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም.(06.05.2012) ነው::

እንደተለመደው ሁሉ ለበዓሉ ተስማሚ በሆኑ ያሬዳዊ ዜማዎች: ቅዳሴና ንግሥ የሚከበር ሲሆን ከቅዳሴ በኋላ የእመቤታችንን ልደት ለማስታወስ ጸበል ጸዲቅ ለየት ባለ መልኩ መናፈሻ ውስጥ የሚደረግ መሆኑን የመስተንግዶ ክፍሉ አስታውቋል::

በስዊዘርላንድና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሁሉ በዚህ እለተ ሰንበት በመገኝት የበረከቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጥሪዋን ታቀርባለች::

Tuesday, April 24, 2012

ማስታወቂያ

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፣ አሜን::

ለዕሑድ ሚያዝያ ሃያ አንድ ቀን (29.04.2012)ተይዞ የነበረው የቅዳሴ መርሃ ግብር የማይኖር መሆኑን በትሕትና እናስታውቃለን::

ሣምንት ሚያዝያ ሃያ ስምንት(06.05.2012)እንደተለመደው የግንቦት ልደታ በዓል በንግሥና ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ስለሚከበር ላልሰሙ ወገኖች እያሰማን እንድንገኝና የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን በእመቤታችን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::

በዙሪክ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም የሰበካ ጉባኤ

Monday, April 16, 2012

የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የ2004 ዓ.ም. ፋሲካ በዓል አከባበር በሥዕል





















በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የፋሲካ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ!










በዙሪክ /ኦፕፊኮን የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዘንድሮው የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በአል እጅግ በጣም ደማቅ በሆነ ሥነ-ሥርአት ተከብሮ ውሏል:: እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስርአት:ከጸሎተ ሓሙስ ጀምሮ የተዘጋጀውን መርሐ ግብር በርካታ ምዕመናን እየተገኙ የበረከቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል::
የዘንድሮው የፋሲካ በአል አከባበርን ካለፉት ዓመታት የተለየ ያደረገው ቁጥሩ እጅግ የበዛ ምዕመን መገኘት ብቻ ሳይሆን በትንሳኤው የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ክ አምስቱ "ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት"ተብለው ከሚታወቁት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ቦታ ካላት)እህት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሕንድና ሶርያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የአውሮጳ ጳጳስ ብጹእ ወዶክተር ሞር አንቲሞስ ማቴዎስ መገኘትና ምዕመናኑን መባረክ ነው::ብጹዕነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት ትንሳኤ ለክርስቲያኖች ያለውን ትርጉም ከገለጹ በኋላ ክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር የሰው ልጆች ቋሚ ጠላት የሆነው ሰይጣንን ጠንክሮ መቋቋምና ድል መንሳትን መቻል ነው ብለዋል::ቀጥለውም ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስላለው ታሪካዊና እምነታዊ ትሥስር አስታውሰዋል::በሰሙትና ባዩት መንፈሳዊነትና በተለይም በያሬዳዊ መዝሙራት ከልብ መደሰታቸውን አልሸሸጉም ብጹእነታቸው::

ጸሎተ ቅዳሴውን የመሩት ዶክተር(MD)ወቀሲስ አየለ ከጸሎተ ሐሙስ እስከ እለተ ትንሳኤው በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አባላት ትጋትና ይልቁንም በትንሿ ስዊዘርላንድ ውስጥ ከቅርብም ከሩቅም የመጣው ቁጥሩ ይኽን ያህል ይሆናል ብለው ባልጠበቁት ምዕመን ብዛትና ተሳትፎ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ቀንአዊነት መደሰታቸውን ና መርካታቸውን ገልጸዋል::




በተመሳሳይ ሁኔታ በጄኔቫ ጸሐዬ ጽድቅ መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የትንሳኤ በአል ከአጎራባች ካንቶኖችና ፈረንሳይም በመጡ በርካታ ምዕመናን አምሮና ደምቆ መከበሩን የሰበካ ጉባኤው አስታውቋል::

Tuesday, April 10, 2012

ሰሞነ ሕማማት በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

ሰሞነ ሕማማት
በኦፕፊኮን/ ዙሪክ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሓሙስ ጀምሮ ክፍት መሆኑንና ሐሙስ ስርዓተ ጸሎት:ዓርብ ሥርዓተ ጸሎትና ስግደት የሚኖር ሲሆን ቅዳሜ ሥዑር ከማታው 2 ሰዓት (8 ፒ ኤም) ጀምሮ ለጌታችንና መድሃኒታችን የትንሳኤ በዓል ተጋባዥ ጳጳስ በሚገኙበት ለበዓሉ ተስማሚ በሆኑ ያሬዳዊ ዝማሬዎችና የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የሚከበር መሆኑን በትሕትና እናበስራለን:: ያልሰሙ ወገኖች ሰምተው የበረከቱ ተሳታፈ እንዲሆኑ የበኩላችሁን እንድታደርጉ ባላደራ መሆናችሁን አትዘንጉ!

Friday, March 23, 2012

ቅዳሴና ትምሕርት በመምሕር ጥበበ ሥላሴ (ከ UK)

ዕሑድ መጋቢት 16 ቀን (25.03.2012) በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴና የስብከተ ወንጌል ትምሕርት የሚኖር መሆኑን የሰበካ ጉባኤው በትሕትና ያስታውቃል:: ቀሲስ (መምሕር) ጥበበ ሥላሴ ከ ታላቋ ብሪታንያ ይመጣሉ::
ምዕመናን ላልሰሙ እያሰማችሁ ሁላችንም የበረከቱ ተሳታፊዎች እንሆን ዘንድ የቸሩ መድሃኔዓለም እርዳታ:የእመቤታችን የድንግል ማርያም ልመናና ጸሎት ከሁላችን ጋር ይሁን!

Wednesday, March 14, 2012

ሰኞ መጋቢት 10 ቀን (19.3.12)የኢትዮጵያ ምሽት በዙሪክ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ይከበራል!

ሰኞ መጋቢት 10 ቀን (19.03.2012)በዙሪክ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ (Stadthaus Zürich
Stadthausquai 17, 8001 Zürich, Switzerland) "የኢትዮጵያ ምሽት" ይከበራል::
በዝግጅቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የዙሪክ መንግሥት ባለሥልጣናትም ጭምር ይገኛሉ:: በዚሁ የኢትዮጵያን ባሕልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ትስስር ለማሳየት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው የረጅም ጊዜ ግንኙነትና ምርምር የሚታወቁት ታዋቂው የ ቴሌቬዥን ጋዜጠኛ ዋልተር ኤገንበርገርና በስዊዘርላንድ የኦርቶዶክሳውያን ማሕበር ዋና ጸሐፊ ያሬድ ሃይለ ሥላሴ ስለኢትዮጵያና የተዋሕዶ እምነት በኢትዮጵያና በዲያስፖራ የሚያሳይ የፊልም ቅንብርና ገለጻ ይቀርባል::

በዚሁ ከ19:00 ጀምሮ በሚከናወነው ዝግጅት ላይ እንድትገኙ ሁላችሁም ተጋብዛችኋል::
አስታውሱ!
ቦታው:- ዙሪክ ማዘጋጃ ቤት
ቀን:- 19.03.2012
ሰዓት:- 19:00

Thursday, February 23, 2012

ለየካቲት ኪዳነ ምሕረት ቅዳሴ በኦፕፊኮን/ዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን















በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
የዙሪክ (ኦፕፊኮን) ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዕሑድ የካቲት 18 ቀን 2004 ዓ.ም (26.2.2012) የኪዳነ ምሕረትን ዓመታዊ በዓል የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሃ ግብር የሚኖር መሆኑን በትሕትና እንገልጻለን:: ላልሰሙ አሰምታችሁ ሁላችንም የበረከቱ ተሳታፊዎች ለመሆን በሰላም ያገናኘን!
የሰበካ ጉባኤው

Thursday, February 16, 2012

ከ "ፍኖተ ጽድቅ" የዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 10ኛ ዓመት ዕትም የተወሰደ:: መልዕክት

እስመ ኢይገድፎ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እስመ ውስተ እዴሁ ኲሉ አጽናፈ ምድር
እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤የምድር ዳርቻወችም በእጁ ውስጥ ናቸው
መዝ :94፣4




ማእምረ ኅቡአት የሆነ እግዚአብሔር የቀደመውን ሰው በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረው ምን ሊያደርግና ምን ሊሆን እንዲሚችል ሳያውቀው ቀርቶ አልነበረም፤ ይልቁንም ሁለት አበይት የሆኑ ሀብታትን ሰጥቶ አከበርው እንጂ፤ እነርሱም 1ኛ፦ የሚያስተውልበትን እውቀት፤ 2ኛ፦ ሙሉ ነፃነት ናቸው ዘዳግም 30፣19 ነገር ግን በገነት በደስታ የመኖር እድል ተስጥቶት የነበረው ሰው እነዚህን ክቡር የሆኑ የእግዚአብሔር ስጦታዎችን በአግባቡ ሊጠቀምባቸው አልቻለም። ይባስ ብሎ ማስተዋልን ለክፉ ምኞት፤ ነፃነቱንም ለጥፋትና ለውርደት ተጠቀመበት መዝ ዳዊት 48፤12። « ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ » ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንድሚጠፉ እንስሶች መሰለ ይላል። በመሰረቱ አዳም በነጻነቱ ምክንያት በራሱ ላይ ላደረሰው ችግር ሁሉ ተጠያቂው ነጻነቱን የሰጠው እግዚአብሔር ሳይሆን በነፃነቱ ያልተጠቀመው አዳም ነው። የሆነው ሆኖ እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም ርስቱንም አይተውምና መዝ፡93፤14 በህገ ልቦና ያመልኩት የነበሩትን ህገ ኦሪት ፤በመጨርሻም ወርዶ ተወልዶ ህገ ወንጌልን በመስጠት በነፃነታችን ምክንያት ያመጣነውን ችግር በቀራንዮ አደባባይ እራሱን አሳልፎ በመስጠት አሰወገደልን።ኢሳ 53፤4 ገላትያ 5፤1

ከዚህ በኋላ ያለው አዲሱ የሰው ልጅ ሕይወት እና ታሪክ ሰው ከሆነው አምላክ ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ የጠበቀና ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና ወንጌልን አስተምሩ ማቴ፤28፤19 ባላቸው ደቀመዛሙርቱ ምክንያት ይህን ዓለም ጨለማ የነበርው ብርሃን፤ ጠማማ የነበረው ቀና፤ ጐምዛዛ የነበረው ጣፋጭ፤ አላዋቂ የነበረው አዋቂ፤ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበርው ባለተስፋ፤ ካጋንንት ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት የተመለሰ ሆነ። መዝ.106፤13-15 በመቀጠልም በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት በመሆኑ የሐዋ ሥራ 8፤1 ከኢየሩሳሌም ውጭ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በአንፆኪያ ተመሰረተች። የሐዋ ሥራ 11፤26

ሀገራችን ኢትዮጵያም በ34ዓ.ም. በጃንደረባው አማካይነት የክርስትና እምነት፤እንዲሁም በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጀምሪያ ደግሞ በከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ የወንጌል ትምህርትና የቤተክርስቲያን ስርዓት ተጠቃሚ በመሆኗ ላለፉት 2000 ዓመታት ታሪኳን፤ ባህሏንና ትውፊቷን በክርስትና ሀይማኖት ላይ መሰረት ያደረገችው ኢትዮጵያ ከቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጋር ያለው አንደነቷ ጸንቶ ቆይቷል። ለወደፊቱም ቀጣይነት እንዲኖረው የአዲሱ ትውልድ ሃላፊነት ነው።
«ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ » እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ መዝሙር 104፤1 እንዳለው ቅዱስ ዳዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሀገር ውጭ ይህንን የካበተ መንፈሳዊ ሀብቷን ለማዳረስ ጥረት ማድረግ ከጀመረች ግማሽ ምዕተ አመት በላይ አስቆጥራለች። ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው መዝሙር 94፤4 እኛም ከአገራችን በብዙ ሺህ ኪሎሜትር ርቀን ብንገኝም በዚህ በስዊዘርላንድ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ግልጋሎቷንና ቡራኬዋን መስጠት ከጀመረች ከ30 ዓመታት በላይ የሆናት ሲሆን በዙሪክ ከተማ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም ስም በተሰየመ ቤተክርስቲያን ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ግን እነሆ ዛሬ 10 ዓመታችንን ሞልተናል። ስለአደረገልን ሁሉ « ይትባረክ እግዚአብሔር አምልከ አበዊነ » ያባቶቻችን አምልክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን እንላለን።
በመጨርሻም የዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ለልጆቿ « ንዑ ንትፈሣሕ በእግዚአብሔር። ወንየብብ ለአምላክነ ወመድኃኒነ። ወንብፃ ቅደመ ገጹ በአሚን ።ወበመዝሙር ንየብብ ሎቱ እስመ አብይ ውእቱ እግዚአብሔር አምላክነ። »
ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን ፤በአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል ፤በምስጋና ወደፊት እንድረስ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል ፤እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና ። መዝ.94፤1-3 በማለት ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ::
መልአከ ገነት አባ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ማርያም (ቆሞስ) በስዊዘርላንድ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ

Thursday, February 9, 2012

ቅዳሴ ዕሑድ የካቲት 4 ቀን / 12.Februar 2012

ዕሑድ የካቲት 11 ቀን (February 19. 2012) በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስትያን እንደተለመደው መደበኛ መርሃ ግብር የሚኖር መሆኑን የሰበካ ጉባኤው በትህትና ያስታውቃል:: አድራሻውን ለGPS ተጠቃሚዎች - Wallisellerstrasse 20, 8152 Glattbrugg or Opfikon መስጠት ይቻላል::

Thursday, February 2, 2012

ዳግመኛ ፍጠረን! - ግጥም (ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም ) የተወሰደ

ዳግመኛ ፍጠረን
"እግዚአብሔርም አለ: ሰውን በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር" ኦ.ዘ.ፍ. 1:26
ቸሩ እግዚአብሔር ፈጣሪ አባታችን
ቢወደን ቢያከብረን ባምሳሉ ፈጠረን
ከቶ እንዳይቸግረን ምንም እንዳይጎድለን
ብዙ ተባዙባት..
ምድርንም ግዙ ብሎ አስረከበን::
ታናሽ ለታላቁ ታዛዥ እንዲሆነው
ታላቁም ታናሹን ከልቡ እንዲወደው
ዘር ቀለም ሃይማኖት ጥቅም ሳይለውጠው
ተፋቅሮ እንዲኖር ሕሊና ቢሰጠው
ምነው ያምላክ ፍጡር መንገዱ ቸገረው?!
"እግዚአብሔርም ሰዎችን በመፍጠሩና በምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረጉ አዘነ: እጅግም ተጸጸተ" ኦ.ዘ.ፍ. 6:5
ለምንስ አያዝን ለምን አይጸጽተው
እሱ እየቀረበን እኛ ስንርቀው
ለቅድስና ፈጥሮን እኛ ስናረክሰው
ተፋቀሩ ሲለን እኛ እየተባላን
ደግ ስሩ ሲለን እኛ እየከፋን
መልካም ፍሬ ተክሎ እጸ በለስ ሲያምረን
ስለምን አያዝን ለምን አይጸጽተው?
ቃየሎች ሲበዙ አቤሎች መንምነው
ለምን አይቆጣ አያስደነግጠው?
አንድ አርጎ ሲፈጥረን እሱ ሳይሰለቸው
የሰው ልጅ መለየት መበታተን ሲያምረው
የሌላው የሌላው የውጭው ሳያንሰው
ደጀ ሰላም ገብቶ ይኽ ክፉ በሽታው
እኚህ አባት ከየት? እኛስ ከየት ናቸው?
ማወቅ ያዳግታል ካነጋገራቸው
ሲዳሞ-ወለጋ-ጉራጌ -ሐረሬ
ጎንደር ወይስ ጎጃም ይሆኑ እንደ ትግሬ?
የት ነው ሀገራቸው? ምንድነው ቋንቋቸው?
ብሎ ሲከፍላቸው
ቃሉን እንዲሰብኩ እሱ ለሾማቸው
ቢያጠፉ ቢያለሙ እሱ ፍርድ እያለው
የሰው ልጅ ዳኝነት ስለምን አማረው?
ካይኑ ውስጥ ምሰሶ ማውጣት ሳይቻለው
የሌላውን ጉድፍ ከቶ በምን አየው?
ከፈጣሪው ቀድሞ መፍጠር ሲከጅለው
እንዴት አይቸገር እንዴት አይጸጽተው!

አንደኛው ሲተጋ ለጽድቅ ለነፍሱ
የጌታ ማደርያ ሲገነባ ዳሱ
ትርጉሙ ምንድነው ሌላኛው ማፍረሱ
ይሄ ይሆን እንዴ
ትንቢቱ ሊፈጸም ሰዓቱ መድረሱ?!
እግዚኦ ፈጣሪ
በዚች አጭር እድሜ ስንቱን አሳየኽን
ስንቱን አስተማርከን በስንቱስ ፈተንከን
ባክህ ተለመነን ባክህ ይቅር በለን
እንደ ቸርነትህ በይቅርታህ ጎብኘን
እንደ ኖህ ከጥፋት በጀልባህ አትርፈን
ከቁጣ አድነህ እባክህ ለውጠን
ስልጣን አለህና ዳግመኛ ፍጠረን::
ከማክዳ በቀለ

ቃለ መጠይቅ - ከ "በስዊዘርላንድ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም 10 ዓመት ክብረ በዓል ልዩ እትም" የተወሰደ

ቃለ መጠይቅ


ስዊዘርላንድ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችበት 10ኛ ዓመትን ለማክበር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን:: ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዴት እና በእነማን ተመሰረተች? ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ እንዲያስረዳን ለቃለ ምልልስ የጋበዝነው አቶ ምሥጢረ ኃይለ ሥላሴን ነው::አቶ ምሥጢረ ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሰበካ ጉባኤው ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ሲያገለግል የቆየና በአሁኑም (አዲሱ)የሰበካ ጉባኤ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ነው::
ከአቶ ምሥጢረ ጋር ቆይታ አድርገው ቃለ ምልልሱን ያጠናቀሩት በቃሉ ተገኘወርቅና ሰሎሞን ረታ ናቸው::

ጥያቄ: የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም እንዴት ተመሰረተች? በእነማን ተመሰረተች?
አቶ ምሥጢረ: ቀደም ሲል እ.አ.አ 1999 ዓ.ም.(በዚህ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ቀናቱ በሙሉ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የተሰጡ ናቸው) በበጋው ወር ልጃችን ማረንን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትና ስርዓት ክርስትና ለማስነሳት ከነበሩን አማራጮች መካከል አንዱ ጄኔቫ የሚቀጥለውን የቅዳሴ ወቅት መጠበቅ (በዚያን ጊዜ ጄኔቫ የሚቀደሰው በዓመት ከሶስት ጊዜ ባልበለጠ ከበለጠም በአጋጣሚ ካህን ለስብሰባ ከመጣ ዲያቆን ከእንግሊዝ አገር ወይም ከኢየሩሳሌም በማስመጣት ነበር)ስለሆነም ወንድ ልጅ በአርባ ቀኑ ሊጠመቅ የሚችልበት መንገድ ቢኖር አጋጣሚ ብቻ ስለነበርና ሌላው አማራጭ ጀርመን/ኮሎኝ ሄዶ ክርስትና ማስነሳት አልያም እንደብዙዎቹ ሁሉ አቅራብያ ወደ ሚገኝ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን መሄድም የሚሉትን ሁሉ ዳስሰን የተሻለ ብለን የመረጥነው ከሆላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑትን አባት ወደ ዙሪክ ጋብዞ ዙሪክ ክርስትና ማስነሳት በሚለው ተስማምተን ቅዳሴው ለመጀመርያ ጊዜ ዙሪክ ውስጥ ተደረገና ሌሎች ሕጻናትም እንዲሁም የ 14 ዓመት ወጣት ክርስትና ተነሳች:: ይህ በራሱ የራሳችን የምንለው ቤተክርስቲያን ቢኖረን ልጆቻችን በስርአቱና በወቅቱ መጠመቅ ብቻ ሳይሆን ለመቁረብም ከዚያም በዘለለ የቤተ ክርስቲያን መኖር በማደግ ላይ የለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ምን ያህል ሊጠቅም እንደሚችል ስለተገነዘብን በዙሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንዲቋቋም ከመመኝትም በላይ መንገዶችን ማመቻቸት አለብን ብለን ወሰንን::

ጥያቄ: ከዚያስ?
አቶ ምሥጢረ: ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር ተአምር ነው ብል ማጋነን እንዳይመስልብኝ እሰጋለሁ:: ቀጣዩ በሙሉ የእግዚአብሔር ተአምር ነው ማለቱ ብቻ የሚሻል ይመስለኛል::

ጥያቄ: ዘርዘር አድርገህ ብትገልጽልን?
አቶ ምሥጢረ: ሰፋ ሊል ይችላል:: እዚህ እኛ የምንኖርበት ቀበሌ ያለው የሪፎሮሚርት ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የ"እንተዋወቅ" ፕሮግራም ነበር:: ያ ፕሮግራም በስደት: በሥራ ምክንያትና በሌሎችም ምክንያቶች አካባቢው ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ እምነቶችና ባሕል ያላቸው ሕዝቦች በአንድ ላይ ተገናኝተው የቻለ የባሕል ምግብ ሰርቶ ይመጣና አንዱ የሌላውን እየቀመሰ የሚተዋወቅበት ቀን ነው ያ ቀን:: እኔና ትልቁ ልጄ ያሬድ በተከታታይ ተገኝተናል ብዙ ሰዎችም ተዋውቀንበታል:: በ2000 ዓ.ም. በነበረው ዝግጅት ላይ ግን አልተገኘንም:: ዘንግተነው ይመስለኛል:: ታድያ የዚያ ዝግጅት አስተባባሪ የሆኑት የሪፎርሚርተው ቄስ ማምሻውን ደውለው ለምን እንደቀረን: ብንመጣ ኖሮ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቄስም ማግኘት እንችል እነደነበረ ቄሱ ከእነ ባለቤታቸው በአቅራቢያችን ከሚገኘው የስደተኞች መኖርያ ውስጥ ነዋሪ ስለሆኑ ስልካቸውን ተቀብየላችኋለሁና ደውሉላቸው ብለው ስልካቸውን ይሰጡናል:: ደወልንላቸው በእውን ሥልጣን ያላቸው ቄስ መሆናቸውንና የመሳሰሉትንም ጠያይቀን ብንኝገናኝስ? ተባባልንና ቤት ውስጥ ያለነው ሁሉ ልናግኛቸው ወድያውኑ ሄደን:: ተገናኘን:: መስቀል አሳልመው አረፍ እንድል ጋብዘው ትንሽ ተጨዋወትንና ለጊዜው ወንጌል ለማስተማር ዝግጁ ነኝ ቦታ ከተገኘ የሚቀጥለው እሁድም ቢሆን ለእኔ መላካም ነው ስላሉን ተደስተን ተለያየን::
ቦታም እዚያው ረፎርሚርተ ቤተክርስቲያን ውስጥ ክፍል ተሰጠንና የምስራቹን እየደወለን በነገሩ ይደሰታሉ ብለን ላመንባቸው ሁሉ ነገርን:: እነሱም እንዲሁ ለሚያውቁት እንዲነግሩ ተስማምተን እሁድ ማርች 12 ቀን 2000 ዓ.ም. ለመጀመርያው ትምሕርት ተገናኘን::ያ እለት የመጀመርያው ቀን ሆነ ማለት ነው::


ጥያቄ: ያ ስብስብ ወደቤተ ክርስቲያንነት እንዴት አደገ? ስያሜውስ እንዴትና ማን ሰየመው?
ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም 4
አቶ ምሥጢረ: ጥሩ ጥያቄ ነው:: ካህን ተገኘ! ለማገልገል ፍጹም ፈቃደኛ ናቸው:: ሌላ ሌላውን ማመቻቸቱ የእግዚአብሔር እርዳታ ከተጨመረበት የእኛ ፋንታ ነው የምንል ሰዎች ተሰባሰብንና ተወያየን:: ቦታ ማግኘቱ የመጀመርያው ሊሆን ይገባዋል ተብሎ ስለታመነበት ያ ሃላፊነት ለእኔ ተሰጠና ስናፈላልግ በመጀመርያ የተሰጠን የሪፎርሚርተው ቦታ ጠባብ በመሆኑ: ግቢ ጠባቂዎቹም እሁድ ገባ ወጣ ማለታችንን ስላልወደዱት አሁን ወደ አለንበት ቦታ እንድንሄድና ሃላፊዎቹን እንድናነጋግር ከቀበሌው አስተዳደር ተጠቁመን ካህኑን (ቀሲስ ፍቅረ ማርያም)ን ይዘን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳዳሪ የሆኑትን ሰው አነጋገርን:: እሳቸውም እላይ ዋናው የነሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግማሹን ከፍለን ለጸሎት ትጠቀሙበታላችሁ ብለው ነበር:: ያ ደግሞ ከስርዓታችን ጋር የማይመች ስለሚሆን ሌላ አማራጭ ካለ ብለን ጠይቀን የተገኘው አሁኑ ቤተ ክርስቲያናችን አድርገን የምንጠቀምበት ቦታ ብቻ ሆነ:: ክፍሉ የወጣቶች የመጫወቻ ክፍል በመሆኑ እነሱ ከሰዓት በኋላ 14 ሰዓት ስለሚገቡ እንደነበረ አድርጋችሁ ታስረክባላችሁ የሚል አማራጭ አገኘን:: አንዳንዶቻችን ያልወደድነው አማራጭ ቢሆንም "ቀሲስ ፍቅረ ማርያም" ስለወደዱት ወደዚያ ያሉንን በጣም ትንሽ እቃዎች አስገባን:: ቦታው የሚጨስበት ልዩ ልዩ ጨዋታዎች እንደ የጠረጴዛ ኳስና ከረንቦላ መጫወቻ ቦታ በመሆኑ የሲጋራውን ቁርጥራጭ ጠራርጎ:ጠረጴዛ እየጎተቱ ቦታ ማስያዝ መልሶ እንደነበረ ማድረግ በተለይም ቦታውን ቤተ ክርስቲያን ማስመሰል የዋዛ ሥራ አልነበረም::
ስያሜው ላይ "መድሃኔ ዓለም" ጄኔቫ ስላለ ሉዘርንም በእመቤታችን ስም አልፎ አልፎም ቢሆን ጸሎት ስለሚደረግ - ቅዱስ ሚካኤል - ቅዱስ ገብርኤል - ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሉት ሁሉ ተነስተው በይበልጥ በካህኑ የትም ቢኖር እዚህም የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊባል ይችላል ብለው " ቅድስት ድንግል ማርያም" የሚለው ተመረጠ::
እንዲያ እንዲያ እያልን ቦታውም የወጣት ክፍል መሆኑ ቀረና ሙሉ በሙሉ (አልፎ አልፎ ለካቶሊክ ወጣቶች ጉዳይ ካልተፈለገ በስተቀር) እንድንጠቀምበት ሆነ:: በመጀመርያ ከጸሓዬ ጽድቅ መድሃኔዓለም (ጄኔቫ) ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት እየተዋስንና ሌላ ሌላም ድጋፍ እየተደረገልን በአባቶች ሜሮን ከተቀባልን በኋላ ቅዳሴ እስከ መቀደስ ተደረሰ:: ውጣ ውረድ ግን ነበረው::
ጥያቄ: ያገጣማችሁ ችግር እንደነበር ሲወራ ሰምተናል:: ምን ነበር? ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ ብለህ የምታምናቸው እንዴትስ ተቀረፉ?
አቶ ምሥጢረ: በመጀመርያ እኛ ከላይ ያልኩህን በጀመርንበት ጊዜ ለስዊስ ቋሚ ካህን ለማምጣት ተሞክሮ እንዳልተሳካ እንሰማ ነበርና እዚህ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን መመስረት እርዳታ ያደርጋል ተብሎ ስለታመነበት ብቻ ሳይሆን በሌላ በሌላ ጉዳዮችም ላይ በጋራ መሥራት እንዳለብን እኛ አምነናል:: ጄኔቫ ከእኛ ቀደም ብሎ ከ 20 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በስዊዘርላንድ ውስጥ በብቸኝነት ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የጸሐየ ጽድቅ መድሃኔ ዓለም ጋር መነጋገር እንዳለብን ስላመንን ለምሳሌ በቅዳሴ ወቅት የሚጠራው የፓትርያርክ ስም ጉዳይና የመሳሰሉትን አንስተን በስዊዘርላንድ ውስጥ ያለው ምዕመን በምንም መልኩ በሌላው ዓለም ውስጥ የሚታየው መከፋፈል እንዳይኖር በየቤተክርስቲያናቱ በጥቅሉ ለጳጳሳቱ- ቀሳውስቱ-ምዕመኑ ከመጸለይ በስተቀር የህ የ እገሌ ነው ያ ደግሞ የእገሌ ነው መባል የለበትም የሚለውን አሳምነን ተቀባይነት አገኘ:: ያ ትልቁ ሊለያየን የሚችል መሰናክል ነበርና በ እግዚአብሔር ቸርነት አለፍነው:: ሌላው ከላይ በቤተ ክርስቲያናችን መቋቋም ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያልኩህ ሰው ጉዳይ ነው:: ወንጌል በማስተማር በኩል ደህና ቢሆኑም ቅስናው ላይ ላይ እጅግም ናቸውና ክሕነታቸውም አጠራጣሪ ነው የሚለው ጉዳይ አብረን ለመቀጠል ስላላስቻለን መለያየት የግድ ሆነ:: እንግዲህ እንደምትገምተው በዚህ ሁኔታ መለያየቱ ቀላል ባለመሆኑ አንዳንድ ጠባሳዎች ለጊዜውም ቢሆን ጥሎ ማለፉ አልቀረም::
የዚያንኑ ያህል ድንቅ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በየጊዜው የሚነሱ ችግሮችን በዘዴና በአርቆ አስተዋይነት ይልቁንም በጽኑ እምነት በመታነጻቸው አልፈናቸዋል::በዚያ ፈታኝ ወቅት የወንጌል ትምሕርት እንዳይቋረጥብን የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ የማይናቅ አገልግሎት ያበረከቱትን ዲያቆን መኮንን ግርማና ዲያቆን ዳንኤል ኃይሉን ማንሳት የግድ ይለኛል:: እዚህ ላይ የሰበካ ጉባኤና በሰንበት ትምሕርት ቤት ታልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ በእመቤታችን ስም ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ:: በተለይም በአሁኑ ጊዜ እዚህ ሀገር ከእኛ ጋር ባይሆኑም ዲያቆን መኮንን ግርማን: አቶ ሰናይ ምንውየለትን; ዶክተር
ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም 5
ርብቃ ፍሥሐንና ዘማሪት ኤልሳ ኢብሳን ሳላነሳ ባልፍ ሕሊናየ እረፍት አያገኝምና መጥቀስ እወዳለሁ::

ጥያቄ: ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብየተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት በተለይም ስዊዘርላንድ ካሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ያለው አንድነት ምን ይመስላል?
አቶ ምሥጢረ : በካንቶን ዙሪክ ካሉ አብየተ ክርስቲያናት ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን:: ቀደም ሲል ገና ቤተ ክርስቲያናችንን ለማቋቋም በወሰነበት ጊዜ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ መልካም ግንኙነት በመመስረታችንም ነው እንዴት ለስዊዘርላንድ አንድ ቋሚ ካህን የሥራ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ምክርና መመርያም ያገኘነው:: በስዊዘርላንድ የአብያተ ክርስቲያናቱ አባል ስንሆን በስዊዘርላንድ ያሉ የኦርቶዶክት ሕብረት (አምስቱ ኦርየንታልና ሩስያ- ሰርቭያ - ግሪክ -ሩማንያ)ሕብረት ለሁለተኛ ጊዜ ዋና ጸሐፊ ሆና ተመርጣ ቤተ ክርስቲያናችን በ ያሬድ ኃይለ ሥላሴ ጸሐፊነት የሥራ አስፈጸሚው አካል ናት::በዙሪኩ የአብያተ ክርስቲያናት አባልነታችንም በኩል ነው ሌላ የተሻለ ቤተ ክርስቲያን የማግኘት ተስፋ አድርገን የምንጠብቀው:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን በሚመለከት በሀገር ስዊዘርላንድ እንዲስፋፋ ለሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ከማድረግ ተቆጥበን አናውቅም:: የሰንበት ትምሕርት ቤቶች እንዲስፋፉ የባለሙያም ሆነ ቁሳቁሳዊ ድጋፍ አድርገናል እናደርጋለን:: ለምሳሌ በርን ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ቦታ እንዲያገኙ ለሚመለከተው ክፍል ደብዳቤ የጻፍነው እኛ ነን:: ከቤተ ክርስቲያኖቻችን አስተዳደሪ እንዲሁም ትልቅ ሥራ በመሥራት ላይ ካለው ከማእከላዊው የሰበካ ጉባኤ ጋር እጅግ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ግንኙነት አለን::

ጥያቄ: ለወደፊቱስ ምን እቅድ አለ?
አቶ ምሥጢረ: የራሳችን የምንለው ቤተ ክርስቲያን በማፈላለግ ላይ ነን:: ፍላጎታችን ትንሽ ሰፋ አለና እስካሁን ለማግኘት ተቸገርን:: ከአንድም ሁለት ሶስት አግኝተን የተውናቸው አሉ:: እኛ እቃ ቤት ያስፈልገናል: ለብቻ ለጸበል ጸዲቅ መቅመሻ የሚሆን ቢቻል አዳራሽ አለበለዝያም ሰፋ ያለ ክፍል እንፈልጋለን:: በዓላታን ስናከብር በማኅሌትና በያሬዳዊ ወረቦችም ከበሮዎቻችንን እንደልባችን እየመታን እልልታው እንደልብ ቀልጦ ማክበሩን እንፈልጋለን ስለዚህም በቀላሉ የማይረበሽ ከመኖርያ ቤቶች ፈንጠር ያለ ቢሆን ይመረጣል:: ይህንን ሁሉ የሚያሟላልን ማግኘት ከባድ ነው:: አምላክ በተአምሩ የቆረቆራትን የእናቱ ስም የሚጠራባትን ቤተ ክርስቲያን እኛ ብናስብም እሱ ቀኑን ቆጥሮ እንደሚያሳካው እምነቴ ነው:: በሌላ በኩል ተጀምሮ የነበረው የአማርኛ ትምሕርት ቤት በቅርቡ ይቀጥላል ብለን አቅደናል:: ቤተ ክርስቲያን ፈልገው ለመጡ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቱ የተለመደ ነው:: ወደ ፊት አቅም እንደፈቀደ እኛም ወጣ ብለን የጠፉትን ከቤተ ክርስቲያን የራቁትን ማምጣትም ይጠበቅብናልና በእቅድ ደረጃ አለ::

ጥያቄ: ለሰጠህን ማብራርያ እናመሰግናለን:: በመጨረሻ ለማስተላለፍ የምትፈልገው መልእክት ካለ?
አቶ ምሥጢረ: አዎን! ለዚህ ያደረሰንን አምላክ አመሰግናለሁ:: አስር ዓመት ብዙ ባይባልም የሚናቅ አይደለም::እክሎች; መሰናክሎች አልነበሩም ማለት አይደለም:: ካቶሊኮች አስጠግተውን: ፐሮቴስታንቶች ይህው ዛሬ አስረኛ በዓላችንን የምናከብርበትን ቦታ ሰጥተውን ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ለ አስረኛ ዓመት በአላችሁ በሰላም ያደረሳችሁ እያሉን ባሉበት ወቅት: በስሙ ክርስቲያን የተባልን የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ በሚቻለው ሁሉ ለመተባበር ስንሞክር በተቃራኒው ለመንጎድ የሚፈልጉትን ስናይ እና ስንሰማ ማዘናችን አልቀረም:: ቤተ መቅደስን ለመገንባት እግዚአብሔር ለፈቀደለት እንጂ እንደ ልቤ ለሚለው ለቅዱስ ዳዊት እንኳን አልሆነም:: እግዚአብሔር በመረጠው መንገድና ሰው ሁሉንም ነገር ያከናውናል:: የሕይወት ተመክሮየ እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም የሚባለውን አባባል ከልቤ እንዳምን አድርጎኛል:: እውነት እንደሚያዋጣ በተደጋጋሚ አይቻለሁ:: ኖሬዋልሁ:: ትዕግሥት ከታከለበት የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ከሆነ የማይቻል የሚመስለው ሁሉ ይቻላል:: እውነት ታሸንፋለችና እንደምታየው ከመሃከላችን ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀናኢ የሆኑትን አምላክ እያስነሳ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገት የሚደረገው ርብርቦሽ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ከውጭ የሚሰሙት እውስጥ ሆነው ከሚያዩት ጋር አልጣጣም እያላቸው እየታዘቡም እያዘኑም ነው:: ለቤተ ክርስቲያኒቱ እላይ ታች የሚሉ አገልጋዮችዋን እግዚአብሔር ይባርክ! ፍቅርና አንድነት ይስጠን::ከዚህ በላይ የምጨምረውም የለኝ ለተሰጠኝ እድል ከልቤ አመሰግናለሁ::

Friday, January 20, 2012

Piniel - New Ethiopian Orthodox Tewahedo Christian Mezmur CD by our very own Zemari Tilahun Abshir



የዘማሪ ጥላሁን አብሽር አዲስ መንፈሳዊ መዝሙር
በስዊዘርላንድ የዙሪክ/ ኦፕፊኮን ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ማሰርያ/መግዣ ይውል ዘንድ የቀረበ! ሲዲውን በመግዛት ቤተ ክርስቲያናችንን ይታደጉ:: ሲዲውን ለመግዛት መካነ ድራችንን ይጎብኙ: ወይም በመልዕክት ማሕደራችን :ethiopian_orthodox@yahoo.de የማዘዣ ቅጽና ዝርዝር መመርያ ያግኙ::

Thursday, January 12, 2012

የአንድ ምእመን ሮሮ

የአንድ ምእመን ሮሮ (ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጦማር የተወሰደ)
(አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትምህርት ይሰጣል፡፡ እኒህ ምእመን ቁጭ ብለው ይሰማሉ፡፡ የሰባኪው ሁኔታ አልጣማቸውምና በልባቸው እንዲህ ያማርራሉ፡፡)

«ምን ገባችሁ ገባችሁ ይላል፤ ይልቅ እንዲገባን አድርጎ አያስተምረንም፡፡ አሁን ኢየሱስ ከናዝሬት ወደ ገሊላ ሄደ ብሎ እልል በሉ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ አሁን እኛ እልል የምንለው ገሊላ ስለ ሄደ ነው፤ ከናዝሬት ስለተነሣ ነው? ወይስ ስለሄደ ነው? እና ላይሄድ ኖሯል፡፡ ለምን ሄደ? እንዴት ሄደ? ሄዶ ምን አገኘን እያለ እንዲነግረን እንጂ ወደ ገሊላ መሄድማ እማሆይ አማረችስ ባለፈው ጊዜ ኢዬሩሳሌምን ሲሳለሙ ገሊላ ሄደው አልነበረም? ወይ አንተ ፈጣሪ፡፡
ልሂድ ልውረድ ልጄንም ላምጣው፣ እያሉ በርእስ መቀለድ ምን የሚሉት አባዜ ነው፡፡ ሰሞኑንማ የእብራይስጥ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈልጋችሁ ያንን ርእስ ካላደረጋችሁ ትታሠራላችሁ የተባላችሁ ነው የምትመስሉት፡፡

አምሳ ዳቦ ከመላስ አንደ ዳቦ መቅመስ አሉ፡፡ አሁን ይህንን ሁሉ ጥቅስ ከመዘርገፍ አንዱን ትንትን አድርጎ ቢያስተምረን አይሻልም፡፡ ስንት ሕፃናት አሉ፡፡ አረጋውያን አሉ፡፡ መጻፍ የማይችሉ አሉ፡፡ ምን ያደርጉታል አሁን፡፡ «ቀላል አይደለንም» ለማለት ካልሆነ በቀር፡፡እኔ የምለው የስብከት ዓላማው ማስተማር መሆኑ ቀርቶ ማዝናናት ሆነ እንዴ፡፡ እነ ክበበው ገዳ ምን ሠርተው ሊበሉ ነው እንዲህ አገልጋዩ ሁሉ ቀልደኛ ከሆነ፡፡ ቅዳሴ ቢያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት አሉ እማሆይ አማረች፡፡ ቆይ አሁን ምን አድርጉ ነው የሚሉን? ኑ ተባልን መጣን፤ አዋጡ ተባልን አዋጣን፤ ጹሙ ተባልን ጾምን፣ ጸልዩ ተባልን ጸለይን፣ ገዳም ሂዱ ተባልን ደርሰን መጣን፣ መጻፍ ግዙ አሉን ገዛን፣ ካሴት ግዙ አሉን ገዛን፣ እልል በሉ ተባልን አልን፣ አጨብጭቡ ተባልን አጨበጨብን፣ አሁንም ይመጡና ኃጢአታ ችሁ ነው ይህንን ሁሉ መዓት ያመጣው ይሉናል፡፡ እሺ ደግሞ ምን ቀረን?አሁን ማን ይሙት ችግር ያለው ከኛ ነው ከእናንተ፡፡ የጥንት ሰዎች ዕድለኞች ሳይሆኑ አልቀሩም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ገድል እና ተአምር ሰምተው ነበር የሚመጡት፡፡ እኛ በናንተ ምክንያት ጭቅጭቅ እና ንትርክ ሆነኮ የምንሰማው፡፡ ስለ ጊዮርጊስ እና ተክለ ሃይማኖት፣ ስለ ጳውሎስ እና ጴጥሮስ፣ ስለ ክርስቶስ ሠምራ እና መስቀል ክብራ መስማት ትተን ስለ ሰባኪ እገሌ እና ሰባኪ እገሌ፣ ስለ እገሌ ቡድን እና እገሌ ቡድን ሆነኮ የምንሰማው፡፡ አይ ስምንተኛው ሺ፡፡
ስምንተኛው ሺ ቢሆን ነው እንጂ የማይጾሙ የሚጾሙትን፣ የማያስቀድሱ የሚያስቀድሱትን፣ የማይፋቀሩ የሚፋቀሩትን፣ ያልጸኑት የጸኑትን፣ የማይቆርቡ የሚቆርቡትን፣ ዓለምን ያልተው ዓለምን የተውትን፣ ያላመኑ ያመኑትን የሚያስተምሩት፤ ሌላ ምን ቢሆን ነው?
አሁን የት እንሂድ? ከዓለም ወደዚህ መጣን፤ ከዘህ ደግሞ ወዴት እንሂድ፡፡ እንዴው ለመሆኑ ስለ ፓትርያርክ፣ ስለ ጳጳስ፣ ስለ ሲኖዶስ፣ ስለ ካህን፣ ስለ ዲያቆን፣ ስለ ባሕታዊ፣ ስለ መነኩሴ፣ ስለ ሰባኪ ደግ ነገር የምንሰማበት ዘመን ይመጣ ይሆን፡፡ ስለ ገዳማት የምንሰማው ሁሉ ተራቡ፣ ተቸገሩ፣ አበምኔቱ ተማሪዎችን አባረሩ፣ መነኮሳቱ አበ ምኔቱን አባረሩ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው ገድል ተጋድለው ተአምር አደረጉ የሚል የምንሰማው፡፡ስለ ጳጳሳት የምንሰማው በራቸው ተደበደበ፣ በሑዳዴ ጾም ከበሮ አስመቱ፣ በሰው ሀገረ ስብከት ገብተው አተራመሱ፣ ቤት ገዙ፣ መኪና ገዙ፣ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው እንደነ ዮሐንስ አፈወርቅ ለእውነት ተጋደሉ የሚል ወሬ የምንሰማው፡፡ ስለ ፓትርያርክ የምንሰማው እገሊት ትመራቸዋለች፣ ሐውልት ሠሩ፣ ውጭ ሀገር ሄደው ተዝናኑ፣ ገንዘብ አባከኑ፣ በዘመድ ሠሩ፣ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው እንደ አትናቴዎስ ለሃይማ ኖታቸው መሥዋዕትነት ከፈሉ፣ እንደ ድሜጥሮስ ተአምር አደረጉ የሚል የምንሰማው፡፡ አልታደልንም መሰል፡፡የጥንት ሰዎች በየ ደብሩ ሊቃውንቱ ምሥጢር እና ቅኔ ሲዘርፉ ነበር አልነበር እንዴ ያሉን፡፡ ምነው በኛ ዘመን ቅኔው ቀርቶ ሙዳየ ምጽዋት ብቻ ሆነ የሚዘረፈው፡፡ በየትምህርቱ ስንሰማ ታሥረው በግንድ፣ ተይዘው በግድ ተሾሙ አይደል እንዴ የምትሉን፡፡ ይኼ የነገራችሁን ነገር ተረት ቢሆን ነው እንጂ እንዴት በኛ ዘመን ሊለወጥ ቻለ ታድያ፡፡አንዳንዴኮ እዚያው ተአምረ ማርያማችንን ብቻ እየሰማን፣ ከግብጽ በሚመጣ አንድ ጳጳስ እየተባረክን ውስጡን ሳናውቀው በቀረን ኖሮ ያሰኛል፡፡ እንዴው እነዚህ ሐዋርያት የሚባሉ ይህንን መጽሐፍ የጻፉት በምን ቀን ነው? የአባቶቻችን ተረት እንኳን ለዛ ነበረው፡፡ ማቴዎስ እንዲህ አለ፤ ሉቃስ ይህንን አለ፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡፡ እሺ አለ፡፡ ደግሞኮ «አያችሁ» ይለናል፡፡ ምኑን ነው የምናየው፡፡ እግዚአብሔርንማ እንዳናየው አንተው ራስህ ጋርደህን፡፡ ምን አስተማረ? መባሉ ቀርቶ ማን አስተማረ ሆነ፡፡ ስንት ሰው ተለወጠ? መሆኑ ቀርቶ ስንት ሰው ተሰበሰበ ሆነ፡፡ እኛ የዚህን ዓለም የአለባበሰ ፋሽን እንድንተው አስተማራችሁን፡፡ እሺ ብለን ትተን ስንመጣ እናንተ የየቀሚሱን ዓይነት ፋሽን አመጣችሁት፡፡ ምንድን ነው ይኼ ሁሉ አሸንክታብ? እናንተ መድረክ ላይ ገዝፋችሁ እየታያችሁ ጌታን በየት እንየው፡፡ የሚነገረው ስለ እናንተ ነው፡፡ «ጸጋ የበዛለት፣ታዋቂ፣ ልዩ፣ ልብ ሰባሪ፣አጥንት ነቅናቂ» ከበሮ ለምን ይጮኻል ቢሉ ውስጡ ባዶ ስለሆነ ነው አሉ አሉ፡፡ ተግባራችሁ ይነግረናልኮ፣ ብዙ ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ እናንተ ስለ እግዚአብሔር ተናገሩ፣ እርሱ ስለ እናንተ ይናገራል፡፡ እናንተ ስለ ራሳችሁ ስለምትናገሩ ግን እርሱን ዝም አሰኛችሁት፡፡እንዲያውም ብዙ ሕዝብ ከሌለ አንመጣም ትላላችሁ አሉ፡፡ ለመሆኑ ይኼ እናንተ የያዛችሁት መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ አንዲት ሳምራዊትን ሴት ለብቻዋ ማስተማሩን አይናገርም ይሆን፡፡ ለመሆኑ ስብከት ለእናንተ ሥራ ነው ወይስ አገልግሎት? ይህንን ሕዝብ ምን እናቅርብለት ብላችሁ ትጨነቃላችሁ? ትጸልያላችሁ፣ ታነባላችሁ? ትጠይቃላችሁ? ወይስ? ምናልባት የማትኖሩበትን ስለምታስ ተምሩን ይሆን መለወጥ ያቃተን? የሌላችሁን ስለምትለግሱን ይሆን ብዛት እንጂ ጥራት ሊኖረን ያልቻለው? ክርስቲያን ታደርጉናላችሁ ብለን ብንመጣ ቲፎዞ አደረጋችሁን፡፡ ለቲፎዞ ለቲፎዞማ አርሴናልና ማንቸስተር ነበሩልንኮ፡፡ ሲገባባቸው ተናደን ሲያገቡ ጨፍረን ቤታችን እንገባ ነበር፡፡ አሁንምኮ እንደዚያ አደረጋችሁት ሁሉም ቲፎዞ ሰብሳቢ ሆነ፡፡ የእገሌ ተከታይ ይባልልኛል፡፡ አስከትላችሁ አስከትላችሁ የት ታደርሱን ይሆን?የታደሉት የዮሐንስ መጥምቅ ተከታዮች መጨረሻቸው ከክርስቶስ ጋር መገናኘት ሆነ፡፡ እኔ ዝቅ ዝቅ ልል እርሱ ግን ከፍ ከፍ ሊል ይገባዋል ብሎ አገናኛቸው፡፡ የርሱ ሥራ ድልድይ መሆን ነበረ፡፡ እኛ የናንተ ተከታዮችስ ታገናኙን ይሆን? ቆይ ግን የሚያስፈልገንን ነው የምትነግሩን ወይስ የምትፈልጉትን? ልታሳውቁን ነው የምትመጡት ወይስ ማወቃችሁን ልትነግሩን፡፡ የምታስተምሩትንስ ታውቁታላችሁ ወይስ ታምኑበታላችሁ?
ቢቻል የምትታዩ ከዋክብት ሁኑልን፣ ባይቻል ደግሞ የማትታዩ ከዋክብት ሁኑ፡፡ ቢቻል አርአያችሁን ምሳሌያችሁን እንድንከተል የምትነግሩንን ብትኖሩት፣ የምታስተምሩትን በእናንተ ብናየው፤ ባይቻል ደግሞ የማታስተምሩንን በእናንተ እንዳናየው ብታደርጉ፡፡
እንዴው ግን እዚህ መሬት ስንቀመጥ የማናውቅ እንመስላችኋለን? እዚህ ቦታኮ በእድሜም በዕውቀትም የምንበልጣችሁ ሰዎች አለን፡፡ አጋጣሚውኮ ነው እናንተን ለመድረክ እኛን ለአግዳሚ ወንበር የዳረገን፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቻችን በትኅትና ምክንያት እንጂ ርእሱን ስትናገሩ እንደ ነጣቂ ባለ ቅኔ መደምደሚያችሁንም እናውቀዋለንኮ፡፡ እኛኮ እየተማርን ያለነው ቃለ እግዚአብሔር ምግብ ስለሆነ ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርኮ ዕውቀት ብቻ አይደለም ብለን ነው፡፡ እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ይናገ ራል ብለን ነው፡፡ተው ብታውቁበት ይሻላል፡፡ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣ ይችላል፡፡ (በዚህ ጊዜ ሰባኪው ትምህርቱን ጨረሰ፡፡ እልል ተባለ ተጨበጨበ)ወይ ግሩም ቀበሌ ክርስትና ተነሥታ እዚህ መጣች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላው ይመጣና ከዚያ የቀጠለ ይሁን፣ የበለጠ ይሁን፣ የተለየ ይሁን፣ ያንን የሚያፈርስ ይሁን፣ የሚቃወም ይሁን ደግሞ ያስተምራል፡፡ እንዴው ሥርዓት የሚያወጣ የለም፡፡ ምነው እንደ ቅዳሴው ግፃዌ ቢሠራለት፡፡ የትኛው ከየትኛው እንደሚቀጥል አይታወቅም?
ያም ይመጣና ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ይሄዳል፣ ይሄም ይመጣና ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ይሄዳል፡፡ ሁልጊዜ ተስፋ እንድንቆርጥ፣ እግዚአብሔር ቀጭ፣መዓት አምጭ፣ ተቆጭ፣ ብቻ ነው እንዴ? መሐሪስ አይደለም፣ ይቅር ባይስ አይደለም፣ ተስፋ ሰጭስ አይደለም፡፡ አንዳንዴኮ የሰባክያን እግዚአብሔር የተለየ እግዚአብሔር ሳይሆን አይቀርም፡፡ እናንተን ዝም ብሎ እኛን ብቻ የሚቀጣበት ምክንያት ምንድን ነው?ችግሩኮ አንደኛው ሰባኪ ሌላው ሲያስተምር አይሰማም፡፡ ሊጨርስ ሲል ይመጣና የተለየ መስሎት ያንኑ ደግሞ ያስተምረናል፤ የባሰው ደግሞ የሚቃወም ነገር ይነግረናል፡፡ እኛም ለሁሉም እናጨበጭባለን፡፡
(ሰባኪው ስለ ራሱ መናገር ሲጀምር) በል ስለ እግዚአብሔር የምትነግረን መስሎኝ ነበር እንጂ ስላንተማ ብዙ ዐውቅ የለ ብለው ምእመኑ ልባቸውን ዘጉ፡፡

Monday, January 2, 2012

የገና በዓል አከባበር በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አርብ ታኅሳስ 27 ቀን በ 1900 ሰዓት ይጀምራል!

የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የ2004 የልደት በዓል (ገና)በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መርሃግብር ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን (6.1.2012) በ1900 ሰዓት ይጀምራል::በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል::

ቀደም ሲል ቀኑንና ሰዓቱን በሚመለከት ተነግሮ የነበረው በዚህ መስተካከሉን በትሕትና እናስታውቃለን:: ላልሰሙ ወገኖች እንድታሰሙ በጌታችንና በመደሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አደራ እንላለን::
በዙሪክ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም የሰበካ ጉባኤ

ስለ ገና በዓል

ስለ ዘንድሮው የገና በዓል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የላኩልንን ይመልከቱ;
---------------------------------------

ታኅሣሥ 28 ቀን፥ 2004 ዓ.ም.
እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ
ልደት የሚከበረው በታኅሣሥ 29፥ በሠግር ዓመት ግን በታኅሣሥ 28 ስለሆነ ዘንድሮ የሚከበረው በታኅሣሥ
28 ቀን ነው።
በሀገራችን የሠግር ዓመት መቼ እንደሆነ የማያውቁ ሰዎች ልደት የሚከበርበት ቀን ይምታታባቸዋል።
አባቶቻችን ለዚህ መፍትሔ ሲፈልጉ ለአራቱ ወንጌላውያን አንድ አንድ ዓመት ሰጥተው ዓመቱን "ዘመነ
ማቴዎስ"፥ "ዘመነ ማርቆስ"፥ "ዘመነ ሉቃስ"፥ "ዘመነ ዮሐንስ" እያሉ ያስኬዱና ዓመቱ እንደ ዘንድሮው
ዘመነ ዮሐንስ ሲሆን ልደት የሚውለው በታኅሣሥ 28 ነው ይሉናል--በአራት ዓመት ወይም በየአራት ዓመቱ
አንዴ ማለታቸው ነው።
ዓመቱ ለምን "ሠግር" ተባለ? "ሠገረ" ፥ "ተሻገረ" የሚሉት የአማርኛ ቃላት "ሠግር" ከሚለው የግዕዝ ቃል
ጋር ዝምድና አላቸው። "ሠግር" ማለት "ተሻጋሪ"፥ "ዘላይ" ማለት ነው። ዓመቱ 365 ቀናት መሆኑ ቀርቶ
366 ቀን ሲሆን ምዕራባውያን "Leap Year" ይሉታል፤ ያው "ዘላይ ዓመት" ማለታቸው ነው። በእኛ
የአቈጣጠር ዘዴ ጳጒሜ 5 ቀናት መሆኗ ቀርቶ 6 ቀን ስትሆን ማለት ነው። ቈጠራው የሚምታታው
"የሠግር ዓመት" የሚባለው ዘመነ ሉቃስ ነው ወይስ ዘመነ ዮሐንስ ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ምክንያቱም
ጳጒሜ 6 ቀናት የምትሆነው በዘመነ ሉቃስ ነው። ልደት በታኅሣሥ 28 የሚውለው ግን በዘመነ ዮሐንስ
ንው።
እኛ ያየነው ጳጒሜ በዘመነ ሉቃስ 6 ቀናት ስትሆን ዘመነ ዮሐንስ የሚጀምርበትን፥ መስከረም 1ን፥
በአንድ ቀን ማስዘግየቷን ነው። አንድ ቀን ታስዘልለውና እንደሌሎቹ ዓመታት በ1 መጀመሩን ትቶ፥ 2
ሊሆን በሚገባው ቀን ይጀምራል። በአዘቦት ዓመታት መስከረም 2 ሊሆን የሚገባውን ቀን መስከረም 1
አለው ማለት ነው። መስከረም አንድ በአንድ ቀን ዘግይቶ ከጀመረ ("ከጀመረ" በማለት ፈንታ "ከባተ"
ይላሉ)፥ ወራቱ ሁሉ (ታኅሣሥን ጨምሮ ማለት ነው) አንድ ቀን እያሳለፉ መጀመር (መባት) ግድ
ይሆንባቸዋል። ልደት አብሮ አይዘገይም፤ ቦታውን እንደያዘ ይኖራል። ስለዚህ በሠግር ዓመት ታኅሣሥ
አንድ ቀን ዘግይቶ እ2 ላይ ከጀመረ ልደት የሚውልበት ታኅሣሥ 29 ቀደም ብሎ በታኅሣሥ 28 ቀን
ይውላል። የሠግር 28 ቀንና የአዘቦቱ 29 ቀን ሁለቱም እኩል ዮናርዮስ 7 (January 7) ናቸው።
ልደትን የምታከብሩ ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያደረሳችሁ።
ጌታቸው ኃይሌ።