ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Thursday, May 9, 2013

 
በኦፊኮን  ደብረ  ገነት  ቅድስት  ድንግል  ማርያም  ቤተ ክርስቲያን
 እንደተለመደው  የልደታ  በዐል  በታላቅ  ሥነ  ስርዓት  ይከበራል!
ቀን ; ግንቦት 4 (12.5.2013)
ሠዐት ከጧቱ 08 ጀምሮ!!
ቦታ; ደብረ ገነት ቅ.ማ. ቤተ ክርስቲያን ኦፕፊኮን

ዕሑድ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. (12.5.13) የግንቦት ልደታ በዐል በታላቅ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ስርዓትና ንግስ ይከበራል

ዕሑድ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. (12.5.13) የግንቦት ልደታ በዐል በታላቅ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ስርዓትና ንግስ ይከበራል።





የትንሣዔ በዐል አከባበር በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በምስል





Friday, May 3, 2013

ስቅለተ ክርስቶስ



ምክንያቱም እግዚአብሔር የሌለበት ሕይወት አይሠምርም ። እግዚብሔርን አሳዝነው ኃጢአትን ሰርተው የሚገኘው በሥጋም በነፍስም መከራና ስቃይ እንጂ ጸጋና ክብር አይደለምና ። አዳምና ሔዋንም ጸጋቸው ተገፎ ፣ክብራቸውንና ሰላማቸውን አጥተው፣ ተቅበዝብዘው ፣ ገነትን የመሰለች ቦታ እግዚአብሔርን የመሰለ ጌታ በማጣታቸውና በመከራ ውስጥ በመውደቃቸው ምክንያት የተነሳ ፣ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ያገኙ ዘንድ ሌት ተቀን በእንባ ወደ እግዚአብሔር ይጮኹ ፣ ይጸልዩ ጀመር ። እግዚአብሔርም እርሱ ዳግማዊ አዳም ሆኖ ፣ ስለ አዳም ክሶ ፣ ከሰይጣን ባርነት ነጻ እንዲያወጣው " ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ " የሚል የተስፋ ቃል ሰጠው ። አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ሆኖ ይህንን የተስፋ ስንቅ ይዞ ሥጋው ወደ መቃብር ወረደ ፤ ነፍሱም በሲኦል 5500 ዘመናት ያህል ኖረች ። እኛስ ስንቶቻችን ነን ለዘመናት በአደባባይም ሆነ ፣ ተደብቀን የሠራነው ኃጢአትና የበደልነው ነገር ሁሉ ዛሬ ንስሐ ባለመግባታችንና ፈጽመን ባለመመለሳችን ምክንያት በኅሊና ጸጸት እየተሰቃየን ነገ ደግሞ ለመከራ ሥጋና ለመከራ ነፍስ ተላልፈን እንደምንሰጥ አውቀን ተረድተን ከኃጢአት ሕይወት ተመልሰን ፣ በእግዚአብሔር ቤት አንድነታችንን ጠብቀን በመኖር ስለበደልነው ሁሉ ለምሕረት ፣ለይቅርታ ወደ አምላካችን በለቅሶና በዋይታ በመቅረብ ልመናችንን የምናሰማ ?

እነሆ ቀደም ሲል ሰይጣን አዳምና ሔዋንን እባብ መስሎ ፣ ራሱን ሰውሮ መጥቶ እንዳሳታቸው ሁሉ ፤ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔርም ጊዜው ሲደርስ በረቂቅ ጥበቡ የሥጋዌን ምሥጢር ከሰይጣን ሰውሮ ፣ የወደቀውንና የተጎሳቆለውን አዳም ከሰይጣን ባርነት ነጻ ለማውጣት ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም ማኅፀን ተወለደ ። እርሱም ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው የሆነ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ዲያብሎስም የዓለም መድኃኒት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር መስሎት ነፍሱን በሲኦል ፣ ሥጋውን በመቃብር ሊቆራኝ ፈልጎ በቀረበ ጊዜ ፣ ጌታችን ግን በአምላክነቱ ኃይል ወጥሮ በመያዝ በስቅለቱና በሞቱ ድል ነስቶታል ። ዲያብሎስም ተሸነፈ ፤ ለ5500 ዘመናት ያህል በሲኦል ውስጥ በአጋንንት እግር ሲቀጠቀጥና ሲሰቃይ የነበረው የአዳም ዘር በሙሉ ነጻ ወጣ ።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በየዓመቱ የስቅለት ቀን በጾም ፣ በጸሎት፣ በስግደትና በተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የምታከብርበት ምክንያት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ የተፈጸመበት ዕለት በማሰብ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመነ ስደቱ ጀምሮ በዕለተ ዓርብ መጋቢት 27 ቀን በመስቀል ላይ ከተሰቀለበትና በፈቃዱ ሞትን እስከ ቀመሰበት ድረስ ስለኛ የተቀበለው መከራ እጅግ ብዙ ነው ። ይህንን መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ጌታችን በዕለተ ስቅለቱ ከተቀበላቸው መከራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን (ሕማማተ መስቀሉን ) አሥራ ሦስት ብለው ቆጥሮአቸዋል ። እነርሱም ፥ ተአስሮ ድኅሪት (እጆቹን የኋሊት መታሰሩ) ፣ ተቀሥፎተ ዘባን( ጀርባውን መገረፉ ) ፣ ወሪቀ ምራቅ ( በላዩ ላይ ምራቃቸውን መትፋታቸው ) ፣ ተኰርዖ ርእስ ( ራሱን በብትር መመታቱ ) ፣ ተጸፍዖ መልትሕት (ፊቱን በጥፊ መመታቱ ) ፣ ጸዊረ መስቀል (መስቀሉን መሸከሙ) ፣ አክሊለ ሦክ (የሾኽ አክሊል መቀዳጀቱ) ፣ ሰትየ ሐሞት ( ሐሞት መጠጣቱ ) ፣ ተቀንዎተ አእዳው ( ሁለቱ የእጆቹ ችንካሮች ) ፣ ተቀንዎተ እግር ( ሁለቱ የእግሮቹ ቅንዋት) እና ርግዘተ ገቦሁ ( ጎኑን በጦር የወጉት) ናቸው ። በዕለተ ዓርብ ያ ሁሉ ግፍና መከራ ሲደርስበት ከቀኑ ከስድስት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ " ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ ? – " አምላኬ ! አምላኬ ! ለምን ተውኽኝ ? " አለና የሰጡትን መራራውን ሆምጣጤ ከጠጣ በኋላ በታላቅ ድምጽ ጮኽና ተፈጸመ ብሎ ሞተ ።

ክቡራን ህዝበ ክርስቲያን ሆይ ! የዓለም ጌታና የዓለም መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለማዊ ሞት ለማዳን በመልዕልተ መስቀል የተሰቀለበትን ቀን ስናስብ በአንድ በኩል በሐዘን ነው ። ምክንያቱም እርሱ ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉም ያለው አምላክ ሲሆን ያን ያህል በሰው አንደበት ሊገለጽ የማይችል መከራ ስለኛ ኃጢአትና በደል ብሎ የተቀበለውን ስናስብ እናዝናለን ። በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ "ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት ። ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው ፤ እስከ ሞትም አደረሰው ። " እንዳለ እኛም እርሱ በስቅለቱና በሞቱ ለኛ ያሳየውንና የገለጸውን ፍቅር ስናስብ ደግሞ ልባችን በአድናቆት በአርምሞ ይሞላል ። ሐዘናችንንና አድናቆታችንን የምንገልጸው ደግሞ ለሰራነው ኃጢአት ንስሐ በመግባት ፣ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ጸንተን በመኖርና መልካም ሥራ በመሥራት ነው እንጂ ሌላ አድናቆታችንም ሆነ ሐዘናችን የምንገልጽበት ነገር የለም ።የመድኃኔ ዓለም በረከትና ረድኤት አይለየን ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዘጋጅ ዲያቆን ብሩክ አስፋው

ከባዝል – ስዊትዘርላንድ

Thursday, May 2, 2013

ፋሲካ በዙሪክ (ኦፕፊኮን) ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

ሰሞነ ሕማማትን በጋራ ፀሎትና ስግደት ዘወትር ከቀኑ 17  ሰዓት ጀምሮ እያሰብን እንገኛለን፣ 

 ፀሎተ ሐሙስ ከጧቱ አራት ሰዓት (10) ጀምሮ ቅዳሴን ጨምሮ ሙሉ ሥነ ስርዓት ይከናወናል። ዐርብ የጌታችንንና የመድሃኒታችንን  የኢየሱስ ክርስቶስን ሕመሙን፣ ስቅለቱነቱን ለእኛ ሲል በሰዎች እጅ የደረሰበትን መከራ በስግደትና በጸሎት ከጥዋቱ ሶስት (9) ሰዓት ጀምሮ እናስበዋለን።

 ቅዳሜ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የትንሣኤ በአል በታላቅ ተዋሕዷዊ ሥነ ስርአት የሚከበር መሆኑኑ ለተወደዱ ምዕመናን እያበሰርን ያልሰሙ ወገኖችን አሰምታችሁ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድትሆኑ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም እናሳስባለን።