ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Thursday, February 2, 2012

ዳግመኛ ፍጠረን! - ግጥም (ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም ) የተወሰደ

ዳግመኛ ፍጠረን
"እግዚአብሔርም አለ: ሰውን በመልካችንና በአምሳላችን እንፍጠር" ኦ.ዘ.ፍ. 1:26
ቸሩ እግዚአብሔር ፈጣሪ አባታችን
ቢወደን ቢያከብረን ባምሳሉ ፈጠረን
ከቶ እንዳይቸግረን ምንም እንዳይጎድለን
ብዙ ተባዙባት..
ምድርንም ግዙ ብሎ አስረከበን::
ታናሽ ለታላቁ ታዛዥ እንዲሆነው
ታላቁም ታናሹን ከልቡ እንዲወደው
ዘር ቀለም ሃይማኖት ጥቅም ሳይለውጠው
ተፋቅሮ እንዲኖር ሕሊና ቢሰጠው
ምነው ያምላክ ፍጡር መንገዱ ቸገረው?!
"እግዚአብሔርም ሰዎችን በመፍጠሩና በምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረጉ አዘነ: እጅግም ተጸጸተ" ኦ.ዘ.ፍ. 6:5
ለምንስ አያዝን ለምን አይጸጽተው
እሱ እየቀረበን እኛ ስንርቀው
ለቅድስና ፈጥሮን እኛ ስናረክሰው
ተፋቀሩ ሲለን እኛ እየተባላን
ደግ ስሩ ሲለን እኛ እየከፋን
መልካም ፍሬ ተክሎ እጸ በለስ ሲያምረን
ስለምን አያዝን ለምን አይጸጽተው?
ቃየሎች ሲበዙ አቤሎች መንምነው
ለምን አይቆጣ አያስደነግጠው?
አንድ አርጎ ሲፈጥረን እሱ ሳይሰለቸው
የሰው ልጅ መለየት መበታተን ሲያምረው
የሌላው የሌላው የውጭው ሳያንሰው
ደጀ ሰላም ገብቶ ይኽ ክፉ በሽታው
እኚህ አባት ከየት? እኛስ ከየት ናቸው?
ማወቅ ያዳግታል ካነጋገራቸው
ሲዳሞ-ወለጋ-ጉራጌ -ሐረሬ
ጎንደር ወይስ ጎጃም ይሆኑ እንደ ትግሬ?
የት ነው ሀገራቸው? ምንድነው ቋንቋቸው?
ብሎ ሲከፍላቸው
ቃሉን እንዲሰብኩ እሱ ለሾማቸው
ቢያጠፉ ቢያለሙ እሱ ፍርድ እያለው
የሰው ልጅ ዳኝነት ስለምን አማረው?
ካይኑ ውስጥ ምሰሶ ማውጣት ሳይቻለው
የሌላውን ጉድፍ ከቶ በምን አየው?
ከፈጣሪው ቀድሞ መፍጠር ሲከጅለው
እንዴት አይቸገር እንዴት አይጸጽተው!

አንደኛው ሲተጋ ለጽድቅ ለነፍሱ
የጌታ ማደርያ ሲገነባ ዳሱ
ትርጉሙ ምንድነው ሌላኛው ማፍረሱ
ይሄ ይሆን እንዴ
ትንቢቱ ሊፈጸም ሰዓቱ መድረሱ?!
እግዚኦ ፈጣሪ
በዚች አጭር እድሜ ስንቱን አሳየኽን
ስንቱን አስተማርከን በስንቱስ ፈተንከን
ባክህ ተለመነን ባክህ ይቅር በለን
እንደ ቸርነትህ በይቅርታህ ጎብኘን
እንደ ኖህ ከጥፋት በጀልባህ አትርፈን
ከቁጣ አድነህ እባክህ ለውጠን
ስልጣን አለህና ዳግመኛ ፍጠረን::
ከማክዳ በቀለ

No comments:

Post a Comment