ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Thursday, February 16, 2012

ከ "ፍኖተ ጽድቅ" የዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 10ኛ ዓመት ዕትም የተወሰደ:: መልዕክት

እስመ ኢይገድፎ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እስመ ውስተ እዴሁ ኲሉ አጽናፈ ምድር
እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤የምድር ዳርቻወችም በእጁ ውስጥ ናቸው
መዝ :94፣4




ማእምረ ኅቡአት የሆነ እግዚአብሔር የቀደመውን ሰው በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረው ምን ሊያደርግና ምን ሊሆን እንዲሚችል ሳያውቀው ቀርቶ አልነበረም፤ ይልቁንም ሁለት አበይት የሆኑ ሀብታትን ሰጥቶ አከበርው እንጂ፤ እነርሱም 1ኛ፦ የሚያስተውልበትን እውቀት፤ 2ኛ፦ ሙሉ ነፃነት ናቸው ዘዳግም 30፣19 ነገር ግን በገነት በደስታ የመኖር እድል ተስጥቶት የነበረው ሰው እነዚህን ክቡር የሆኑ የእግዚአብሔር ስጦታዎችን በአግባቡ ሊጠቀምባቸው አልቻለም። ይባስ ብሎ ማስተዋልን ለክፉ ምኞት፤ ነፃነቱንም ለጥፋትና ለውርደት ተጠቀመበት መዝ ዳዊት 48፤12። « ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ » ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንድሚጠፉ እንስሶች መሰለ ይላል። በመሰረቱ አዳም በነጻነቱ ምክንያት በራሱ ላይ ላደረሰው ችግር ሁሉ ተጠያቂው ነጻነቱን የሰጠው እግዚአብሔር ሳይሆን በነፃነቱ ያልተጠቀመው አዳም ነው። የሆነው ሆኖ እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም ርስቱንም አይተውምና መዝ፡93፤14 በህገ ልቦና ያመልኩት የነበሩትን ህገ ኦሪት ፤በመጨርሻም ወርዶ ተወልዶ ህገ ወንጌልን በመስጠት በነፃነታችን ምክንያት ያመጣነውን ችግር በቀራንዮ አደባባይ እራሱን አሳልፎ በመስጠት አሰወገደልን።ኢሳ 53፤4 ገላትያ 5፤1

ከዚህ በኋላ ያለው አዲሱ የሰው ልጅ ሕይወት እና ታሪክ ሰው ከሆነው አምላክ ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ የጠበቀና ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና ወንጌልን አስተምሩ ማቴ፤28፤19 ባላቸው ደቀመዛሙርቱ ምክንያት ይህን ዓለም ጨለማ የነበርው ብርሃን፤ ጠማማ የነበረው ቀና፤ ጐምዛዛ የነበረው ጣፋጭ፤ አላዋቂ የነበረው አዋቂ፤ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበርው ባለተስፋ፤ ካጋንንት ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት የተመለሰ ሆነ። መዝ.106፤13-15 በመቀጠልም በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት በመሆኑ የሐዋ ሥራ 8፤1 ከኢየሩሳሌም ውጭ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በአንፆኪያ ተመሰረተች። የሐዋ ሥራ 11፤26

ሀገራችን ኢትዮጵያም በ34ዓ.ም. በጃንደረባው አማካይነት የክርስትና እምነት፤እንዲሁም በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጀምሪያ ደግሞ በከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ የወንጌል ትምህርትና የቤተክርስቲያን ስርዓት ተጠቃሚ በመሆኗ ላለፉት 2000 ዓመታት ታሪኳን፤ ባህሏንና ትውፊቷን በክርስትና ሀይማኖት ላይ መሰረት ያደረገችው ኢትዮጵያ ከቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጋር ያለው አንደነቷ ጸንቶ ቆይቷል። ለወደፊቱም ቀጣይነት እንዲኖረው የአዲሱ ትውልድ ሃላፊነት ነው።
«ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ » እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ ለአሕዛብም ሥራውን ንገሩ መዝሙር 104፤1 እንዳለው ቅዱስ ዳዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሀገር ውጭ ይህንን የካበተ መንፈሳዊ ሀብቷን ለማዳረስ ጥረት ማድረግ ከጀመረች ግማሽ ምዕተ አመት በላይ አስቆጥራለች። ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው መዝሙር 94፤4 እኛም ከአገራችን በብዙ ሺህ ኪሎሜትር ርቀን ብንገኝም በዚህ በስዊዘርላንድ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ግልጋሎቷንና ቡራኬዋን መስጠት ከጀመረች ከ30 ዓመታት በላይ የሆናት ሲሆን በዙሪክ ከተማ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማሪያም ስም በተሰየመ ቤተክርስቲያን ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ግን እነሆ ዛሬ 10 ዓመታችንን ሞልተናል። ስለአደረገልን ሁሉ « ይትባረክ እግዚአብሔር አምልከ አበዊነ » ያባቶቻችን አምልክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን እንላለን።
በመጨርሻም የዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ለልጆቿ « ንዑ ንትፈሣሕ በእግዚአብሔር። ወንየብብ ለአምላክነ ወመድኃኒነ። ወንብፃ ቅደመ ገጹ በአሚን ።ወበመዝሙር ንየብብ ሎቱ እስመ አብይ ውእቱ እግዚአብሔር አምላክነ። »
ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን ፤በአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል ፤በምስጋና ወደፊት እንድረስ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል ፤እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና ። መዝ.94፤1-3 በማለት ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ::
መልአከ ገነት አባ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ማርያም (ቆሞስ) በስዊዘርላንድ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ

No comments:

Post a Comment