ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Thursday, February 2, 2012

ቃለ መጠይቅ - ከ "በስዊዘርላንድ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም 10 ዓመት ክብረ በዓል ልዩ እትም" የተወሰደ

ቃለ መጠይቅ


ስዊዘርላንድ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችበት 10ኛ ዓመትን ለማክበር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን:: ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዴት እና በእነማን ተመሰረተች? ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ እንዲያስረዳን ለቃለ ምልልስ የጋበዝነው አቶ ምሥጢረ ኃይለ ሥላሴን ነው::አቶ ምሥጢረ ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሰበካ ጉባኤው ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ሲያገለግል የቆየና በአሁኑም (አዲሱ)የሰበካ ጉባኤ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ነው::
ከአቶ ምሥጢረ ጋር ቆይታ አድርገው ቃለ ምልልሱን ያጠናቀሩት በቃሉ ተገኘወርቅና ሰሎሞን ረታ ናቸው::

ጥያቄ: የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም እንዴት ተመሰረተች? በእነማን ተመሰረተች?
አቶ ምሥጢረ: ቀደም ሲል እ.አ.አ 1999 ዓ.ም.(በዚህ ቃለ መጠይቅ ውስጥ ቀናቱ በሙሉ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የተሰጡ ናቸው) በበጋው ወር ልጃችን ማረንን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትና ስርዓት ክርስትና ለማስነሳት ከነበሩን አማራጮች መካከል አንዱ ጄኔቫ የሚቀጥለውን የቅዳሴ ወቅት መጠበቅ (በዚያን ጊዜ ጄኔቫ የሚቀደሰው በዓመት ከሶስት ጊዜ ባልበለጠ ከበለጠም በአጋጣሚ ካህን ለስብሰባ ከመጣ ዲያቆን ከእንግሊዝ አገር ወይም ከኢየሩሳሌም በማስመጣት ነበር)ስለሆነም ወንድ ልጅ በአርባ ቀኑ ሊጠመቅ የሚችልበት መንገድ ቢኖር አጋጣሚ ብቻ ስለነበርና ሌላው አማራጭ ጀርመን/ኮሎኝ ሄዶ ክርስትና ማስነሳት አልያም እንደብዙዎቹ ሁሉ አቅራብያ ወደ ሚገኝ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን መሄድም የሚሉትን ሁሉ ዳስሰን የተሻለ ብለን የመረጥነው ከሆላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑትን አባት ወደ ዙሪክ ጋብዞ ዙሪክ ክርስትና ማስነሳት በሚለው ተስማምተን ቅዳሴው ለመጀመርያ ጊዜ ዙሪክ ውስጥ ተደረገና ሌሎች ሕጻናትም እንዲሁም የ 14 ዓመት ወጣት ክርስትና ተነሳች:: ይህ በራሱ የራሳችን የምንለው ቤተክርስቲያን ቢኖረን ልጆቻችን በስርአቱና በወቅቱ መጠመቅ ብቻ ሳይሆን ለመቁረብም ከዚያም በዘለለ የቤተ ክርስቲያን መኖር በማደግ ላይ የለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ምን ያህል ሊጠቅም እንደሚችል ስለተገነዘብን በዙሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንዲቋቋም ከመመኝትም በላይ መንገዶችን ማመቻቸት አለብን ብለን ወሰንን::

ጥያቄ: ከዚያስ?
አቶ ምሥጢረ: ከዚያ በኋላ የሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር ተአምር ነው ብል ማጋነን እንዳይመስልብኝ እሰጋለሁ:: ቀጣዩ በሙሉ የእግዚአብሔር ተአምር ነው ማለቱ ብቻ የሚሻል ይመስለኛል::

ጥያቄ: ዘርዘር አድርገህ ብትገልጽልን?
አቶ ምሥጢረ: ሰፋ ሊል ይችላል:: እዚህ እኛ የምንኖርበት ቀበሌ ያለው የሪፎሮሚርት ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የ"እንተዋወቅ" ፕሮግራም ነበር:: ያ ፕሮግራም በስደት: በሥራ ምክንያትና በሌሎችም ምክንያቶች አካባቢው ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ እምነቶችና ባሕል ያላቸው ሕዝቦች በአንድ ላይ ተገናኝተው የቻለ የባሕል ምግብ ሰርቶ ይመጣና አንዱ የሌላውን እየቀመሰ የሚተዋወቅበት ቀን ነው ያ ቀን:: እኔና ትልቁ ልጄ ያሬድ በተከታታይ ተገኝተናል ብዙ ሰዎችም ተዋውቀንበታል:: በ2000 ዓ.ም. በነበረው ዝግጅት ላይ ግን አልተገኘንም:: ዘንግተነው ይመስለኛል:: ታድያ የዚያ ዝግጅት አስተባባሪ የሆኑት የሪፎርሚርተው ቄስ ማምሻውን ደውለው ለምን እንደቀረን: ብንመጣ ኖሮ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቄስም ማግኘት እንችል እነደነበረ ቄሱ ከእነ ባለቤታቸው በአቅራቢያችን ከሚገኘው የስደተኞች መኖርያ ውስጥ ነዋሪ ስለሆኑ ስልካቸውን ተቀብየላችኋለሁና ደውሉላቸው ብለው ስልካቸውን ይሰጡናል:: ደወልንላቸው በእውን ሥልጣን ያላቸው ቄስ መሆናቸውንና የመሳሰሉትንም ጠያይቀን ብንኝገናኝስ? ተባባልንና ቤት ውስጥ ያለነው ሁሉ ልናግኛቸው ወድያውኑ ሄደን:: ተገናኘን:: መስቀል አሳልመው አረፍ እንድል ጋብዘው ትንሽ ተጨዋወትንና ለጊዜው ወንጌል ለማስተማር ዝግጁ ነኝ ቦታ ከተገኘ የሚቀጥለው እሁድም ቢሆን ለእኔ መላካም ነው ስላሉን ተደስተን ተለያየን::
ቦታም እዚያው ረፎርሚርተ ቤተክርስቲያን ውስጥ ክፍል ተሰጠንና የምስራቹን እየደወለን በነገሩ ይደሰታሉ ብለን ላመንባቸው ሁሉ ነገርን:: እነሱም እንዲሁ ለሚያውቁት እንዲነግሩ ተስማምተን እሁድ ማርች 12 ቀን 2000 ዓ.ም. ለመጀመርያው ትምሕርት ተገናኘን::ያ እለት የመጀመርያው ቀን ሆነ ማለት ነው::


ጥያቄ: ያ ስብስብ ወደቤተ ክርስቲያንነት እንዴት አደገ? ስያሜውስ እንዴትና ማን ሰየመው?
ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም 4
አቶ ምሥጢረ: ጥሩ ጥያቄ ነው:: ካህን ተገኘ! ለማገልገል ፍጹም ፈቃደኛ ናቸው:: ሌላ ሌላውን ማመቻቸቱ የእግዚአብሔር እርዳታ ከተጨመረበት የእኛ ፋንታ ነው የምንል ሰዎች ተሰባሰብንና ተወያየን:: ቦታ ማግኘቱ የመጀመርያው ሊሆን ይገባዋል ተብሎ ስለታመነበት ያ ሃላፊነት ለእኔ ተሰጠና ስናፈላልግ በመጀመርያ የተሰጠን የሪፎርሚርተው ቦታ ጠባብ በመሆኑ: ግቢ ጠባቂዎቹም እሁድ ገባ ወጣ ማለታችንን ስላልወደዱት አሁን ወደ አለንበት ቦታ እንድንሄድና ሃላፊዎቹን እንድናነጋግር ከቀበሌው አስተዳደር ተጠቁመን ካህኑን (ቀሲስ ፍቅረ ማርያም)ን ይዘን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳዳሪ የሆኑትን ሰው አነጋገርን:: እሳቸውም እላይ ዋናው የነሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግማሹን ከፍለን ለጸሎት ትጠቀሙበታላችሁ ብለው ነበር:: ያ ደግሞ ከስርዓታችን ጋር የማይመች ስለሚሆን ሌላ አማራጭ ካለ ብለን ጠይቀን የተገኘው አሁኑ ቤተ ክርስቲያናችን አድርገን የምንጠቀምበት ቦታ ብቻ ሆነ:: ክፍሉ የወጣቶች የመጫወቻ ክፍል በመሆኑ እነሱ ከሰዓት በኋላ 14 ሰዓት ስለሚገቡ እንደነበረ አድርጋችሁ ታስረክባላችሁ የሚል አማራጭ አገኘን:: አንዳንዶቻችን ያልወደድነው አማራጭ ቢሆንም "ቀሲስ ፍቅረ ማርያም" ስለወደዱት ወደዚያ ያሉንን በጣም ትንሽ እቃዎች አስገባን:: ቦታው የሚጨስበት ልዩ ልዩ ጨዋታዎች እንደ የጠረጴዛ ኳስና ከረንቦላ መጫወቻ ቦታ በመሆኑ የሲጋራውን ቁርጥራጭ ጠራርጎ:ጠረጴዛ እየጎተቱ ቦታ ማስያዝ መልሶ እንደነበረ ማድረግ በተለይም ቦታውን ቤተ ክርስቲያን ማስመሰል የዋዛ ሥራ አልነበረም::
ስያሜው ላይ "መድሃኔ ዓለም" ጄኔቫ ስላለ ሉዘርንም በእመቤታችን ስም አልፎ አልፎም ቢሆን ጸሎት ስለሚደረግ - ቅዱስ ሚካኤል - ቅዱስ ገብርኤል - ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሉት ሁሉ ተነስተው በይበልጥ በካህኑ የትም ቢኖር እዚህም የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊባል ይችላል ብለው " ቅድስት ድንግል ማርያም" የሚለው ተመረጠ::
እንዲያ እንዲያ እያልን ቦታውም የወጣት ክፍል መሆኑ ቀረና ሙሉ በሙሉ (አልፎ አልፎ ለካቶሊክ ወጣቶች ጉዳይ ካልተፈለገ በስተቀር) እንድንጠቀምበት ሆነ:: በመጀመርያ ከጸሓዬ ጽድቅ መድሃኔዓለም (ጄኔቫ) ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት እየተዋስንና ሌላ ሌላም ድጋፍ እየተደረገልን በአባቶች ሜሮን ከተቀባልን በኋላ ቅዳሴ እስከ መቀደስ ተደረሰ:: ውጣ ውረድ ግን ነበረው::
ጥያቄ: ያገጣማችሁ ችግር እንደነበር ሲወራ ሰምተናል:: ምን ነበር? ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ ብለህ የምታምናቸው እንዴትስ ተቀረፉ?
አቶ ምሥጢረ: በመጀመርያ እኛ ከላይ ያልኩህን በጀመርንበት ጊዜ ለስዊስ ቋሚ ካህን ለማምጣት ተሞክሮ እንዳልተሳካ እንሰማ ነበርና እዚህ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን መመስረት እርዳታ ያደርጋል ተብሎ ስለታመነበት ብቻ ሳይሆን በሌላ በሌላ ጉዳዮችም ላይ በጋራ መሥራት እንዳለብን እኛ አምነናል:: ጄኔቫ ከእኛ ቀደም ብሎ ከ 20 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በስዊዘርላንድ ውስጥ በብቸኝነት ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የጸሐየ ጽድቅ መድሃኔ ዓለም ጋር መነጋገር እንዳለብን ስላመንን ለምሳሌ በቅዳሴ ወቅት የሚጠራው የፓትርያርክ ስም ጉዳይና የመሳሰሉትን አንስተን በስዊዘርላንድ ውስጥ ያለው ምዕመን በምንም መልኩ በሌላው ዓለም ውስጥ የሚታየው መከፋፈል እንዳይኖር በየቤተክርስቲያናቱ በጥቅሉ ለጳጳሳቱ- ቀሳውስቱ-ምዕመኑ ከመጸለይ በስተቀር የህ የ እገሌ ነው ያ ደግሞ የእገሌ ነው መባል የለበትም የሚለውን አሳምነን ተቀባይነት አገኘ:: ያ ትልቁ ሊለያየን የሚችል መሰናክል ነበርና በ እግዚአብሔር ቸርነት አለፍነው:: ሌላው ከላይ በቤተ ክርስቲያናችን መቋቋም ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያልኩህ ሰው ጉዳይ ነው:: ወንጌል በማስተማር በኩል ደህና ቢሆኑም ቅስናው ላይ ላይ እጅግም ናቸውና ክሕነታቸውም አጠራጣሪ ነው የሚለው ጉዳይ አብረን ለመቀጠል ስላላስቻለን መለያየት የግድ ሆነ:: እንግዲህ እንደምትገምተው በዚህ ሁኔታ መለያየቱ ቀላል ባለመሆኑ አንዳንድ ጠባሳዎች ለጊዜውም ቢሆን ጥሎ ማለፉ አልቀረም::
የዚያንኑ ያህል ድንቅ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በየጊዜው የሚነሱ ችግሮችን በዘዴና በአርቆ አስተዋይነት ይልቁንም በጽኑ እምነት በመታነጻቸው አልፈናቸዋል::በዚያ ፈታኝ ወቅት የወንጌል ትምሕርት እንዳይቋረጥብን የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ የማይናቅ አገልግሎት ያበረከቱትን ዲያቆን መኮንን ግርማና ዲያቆን ዳንኤል ኃይሉን ማንሳት የግድ ይለኛል:: እዚህ ላይ የሰበካ ጉባኤና በሰንበት ትምሕርት ቤት ታልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ በእመቤታችን ስም ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ:: በተለይም በአሁኑ ጊዜ እዚህ ሀገር ከእኛ ጋር ባይሆኑም ዲያቆን መኮንን ግርማን: አቶ ሰናይ ምንውየለትን; ዶክተር
ነሐሴ 2002 - ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም ኦፕፊኮን/ ዙሪክ 10ኛ ዓመት -ልዩ እትም 5
ርብቃ ፍሥሐንና ዘማሪት ኤልሳ ኢብሳን ሳላነሳ ባልፍ ሕሊናየ እረፍት አያገኝምና መጥቀስ እወዳለሁ::

ጥያቄ: ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብየተ ክርስቲያናት ጋር ያላት ግንኙነት በተለይም ስዊዘርላንድ ካሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ያለው አንድነት ምን ይመስላል?
አቶ ምሥጢረ : በካንቶን ዙሪክ ካሉ አብየተ ክርስቲያናት ጋር በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን:: ቀደም ሲል ገና ቤተ ክርስቲያናችንን ለማቋቋም በወሰነበት ጊዜ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ መልካም ግንኙነት በመመስረታችንም ነው እንዴት ለስዊዘርላንድ አንድ ቋሚ ካህን የሥራ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ምክርና መመርያም ያገኘነው:: በስዊዘርላንድ የአብያተ ክርስቲያናቱ አባል ስንሆን በስዊዘርላንድ ያሉ የኦርቶዶክት ሕብረት (አምስቱ ኦርየንታልና ሩስያ- ሰርቭያ - ግሪክ -ሩማንያ)ሕብረት ለሁለተኛ ጊዜ ዋና ጸሐፊ ሆና ተመርጣ ቤተ ክርስቲያናችን በ ያሬድ ኃይለ ሥላሴ ጸሐፊነት የሥራ አስፈጸሚው አካል ናት::በዙሪኩ የአብያተ ክርስቲያናት አባልነታችንም በኩል ነው ሌላ የተሻለ ቤተ ክርስቲያን የማግኘት ተስፋ አድርገን የምንጠብቀው:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን በሚመለከት በሀገር ስዊዘርላንድ እንዲስፋፋ ለሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ከማድረግ ተቆጥበን አናውቅም:: የሰንበት ትምሕርት ቤቶች እንዲስፋፉ የባለሙያም ሆነ ቁሳቁሳዊ ድጋፍ አድርገናል እናደርጋለን:: ለምሳሌ በርን ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ቦታ እንዲያገኙ ለሚመለከተው ክፍል ደብዳቤ የጻፍነው እኛ ነን:: ከቤተ ክርስቲያኖቻችን አስተዳደሪ እንዲሁም ትልቅ ሥራ በመሥራት ላይ ካለው ከማእከላዊው የሰበካ ጉባኤ ጋር እጅግ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ግንኙነት አለን::

ጥያቄ: ለወደፊቱስ ምን እቅድ አለ?
አቶ ምሥጢረ: የራሳችን የምንለው ቤተ ክርስቲያን በማፈላለግ ላይ ነን:: ፍላጎታችን ትንሽ ሰፋ አለና እስካሁን ለማግኘት ተቸገርን:: ከአንድም ሁለት ሶስት አግኝተን የተውናቸው አሉ:: እኛ እቃ ቤት ያስፈልገናል: ለብቻ ለጸበል ጸዲቅ መቅመሻ የሚሆን ቢቻል አዳራሽ አለበለዝያም ሰፋ ያለ ክፍል እንፈልጋለን:: በዓላታን ስናከብር በማኅሌትና በያሬዳዊ ወረቦችም ከበሮዎቻችንን እንደልባችን እየመታን እልልታው እንደልብ ቀልጦ ማክበሩን እንፈልጋለን ስለዚህም በቀላሉ የማይረበሽ ከመኖርያ ቤቶች ፈንጠር ያለ ቢሆን ይመረጣል:: ይህንን ሁሉ የሚያሟላልን ማግኘት ከባድ ነው:: አምላክ በተአምሩ የቆረቆራትን የእናቱ ስም የሚጠራባትን ቤተ ክርስቲያን እኛ ብናስብም እሱ ቀኑን ቆጥሮ እንደሚያሳካው እምነቴ ነው:: በሌላ በኩል ተጀምሮ የነበረው የአማርኛ ትምሕርት ቤት በቅርቡ ይቀጥላል ብለን አቅደናል:: ቤተ ክርስቲያን ፈልገው ለመጡ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቱ የተለመደ ነው:: ወደ ፊት አቅም እንደፈቀደ እኛም ወጣ ብለን የጠፉትን ከቤተ ክርስቲያን የራቁትን ማምጣትም ይጠበቅብናልና በእቅድ ደረጃ አለ::

ጥያቄ: ለሰጠህን ማብራርያ እናመሰግናለን:: በመጨረሻ ለማስተላለፍ የምትፈልገው መልእክት ካለ?
አቶ ምሥጢረ: አዎን! ለዚህ ያደረሰንን አምላክ አመሰግናለሁ:: አስር ዓመት ብዙ ባይባልም የሚናቅ አይደለም::እክሎች; መሰናክሎች አልነበሩም ማለት አይደለም:: ካቶሊኮች አስጠግተውን: ፐሮቴስታንቶች ይህው ዛሬ አስረኛ በዓላችንን የምናከብርበትን ቦታ ሰጥተውን ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ለ አስረኛ ዓመት በአላችሁ በሰላም ያደረሳችሁ እያሉን ባሉበት ወቅት: በስሙ ክርስቲያን የተባልን የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ በሚቻለው ሁሉ ለመተባበር ስንሞክር በተቃራኒው ለመንጎድ የሚፈልጉትን ስናይ እና ስንሰማ ማዘናችን አልቀረም:: ቤተ መቅደስን ለመገንባት እግዚአብሔር ለፈቀደለት እንጂ እንደ ልቤ ለሚለው ለቅዱስ ዳዊት እንኳን አልሆነም:: እግዚአብሔር በመረጠው መንገድና ሰው ሁሉንም ነገር ያከናውናል:: የሕይወት ተመክሮየ እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም የሚባለውን አባባል ከልቤ እንዳምን አድርጎኛል:: እውነት እንደሚያዋጣ በተደጋጋሚ አይቻለሁ:: ኖሬዋልሁ:: ትዕግሥት ከታከለበት የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ከሆነ የማይቻል የሚመስለው ሁሉ ይቻላል:: እውነት ታሸንፋለችና እንደምታየው ከመሃከላችን ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀናኢ የሆኑትን አምላክ እያስነሳ ዛሬ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገት የሚደረገው ርብርቦሽ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ከውጭ የሚሰሙት እውስጥ ሆነው ከሚያዩት ጋር አልጣጣም እያላቸው እየታዘቡም እያዘኑም ነው:: ለቤተ ክርስቲያኒቱ እላይ ታች የሚሉ አገልጋዮችዋን እግዚአብሔር ይባርክ! ፍቅርና አንድነት ይስጠን::ከዚህ በላይ የምጨምረውም የለኝ ለተሰጠኝ እድል ከልቤ አመሰግናለሁ::

No comments:

Post a Comment