ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Friday, January 20, 2012

Piniel - New Ethiopian Orthodox Tewahedo Christian Mezmur CD by our very own Zemari Tilahun Abshir



የዘማሪ ጥላሁን አብሽር አዲስ መንፈሳዊ መዝሙር
በስዊዘርላንድ የዙሪክ/ ኦፕፊኮን ደብረ ገነት ቅድስት ድንግል ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ማሰርያ/መግዣ ይውል ዘንድ የቀረበ! ሲዲውን በመግዛት ቤተ ክርስቲያናችንን ይታደጉ:: ሲዲውን ለመግዛት መካነ ድራችንን ይጎብኙ: ወይም በመልዕክት ማሕደራችን :ethiopian_orthodox@yahoo.de የማዘዣ ቅጽና ዝርዝር መመርያ ያግኙ::

Thursday, January 12, 2012

የአንድ ምእመን ሮሮ

የአንድ ምእመን ሮሮ (ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጦማር የተወሰደ)
(አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትምህርት ይሰጣል፡፡ እኒህ ምእመን ቁጭ ብለው ይሰማሉ፡፡ የሰባኪው ሁኔታ አልጣማቸውምና በልባቸው እንዲህ ያማርራሉ፡፡)

«ምን ገባችሁ ገባችሁ ይላል፤ ይልቅ እንዲገባን አድርጎ አያስተምረንም፡፡ አሁን ኢየሱስ ከናዝሬት ወደ ገሊላ ሄደ ብሎ እልል በሉ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ አሁን እኛ እልል የምንለው ገሊላ ስለ ሄደ ነው፤ ከናዝሬት ስለተነሣ ነው? ወይስ ስለሄደ ነው? እና ላይሄድ ኖሯል፡፡ ለምን ሄደ? እንዴት ሄደ? ሄዶ ምን አገኘን እያለ እንዲነግረን እንጂ ወደ ገሊላ መሄድማ እማሆይ አማረችስ ባለፈው ጊዜ ኢዬሩሳሌምን ሲሳለሙ ገሊላ ሄደው አልነበረም? ወይ አንተ ፈጣሪ፡፡
ልሂድ ልውረድ ልጄንም ላምጣው፣ እያሉ በርእስ መቀለድ ምን የሚሉት አባዜ ነው፡፡ ሰሞኑንማ የእብራይስጥ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈልጋችሁ ያንን ርእስ ካላደረጋችሁ ትታሠራላችሁ የተባላችሁ ነው የምትመስሉት፡፡

አምሳ ዳቦ ከመላስ አንደ ዳቦ መቅመስ አሉ፡፡ አሁን ይህንን ሁሉ ጥቅስ ከመዘርገፍ አንዱን ትንትን አድርጎ ቢያስተምረን አይሻልም፡፡ ስንት ሕፃናት አሉ፡፡ አረጋውያን አሉ፡፡ መጻፍ የማይችሉ አሉ፡፡ ምን ያደርጉታል አሁን፡፡ «ቀላል አይደለንም» ለማለት ካልሆነ በቀር፡፡እኔ የምለው የስብከት ዓላማው ማስተማር መሆኑ ቀርቶ ማዝናናት ሆነ እንዴ፡፡ እነ ክበበው ገዳ ምን ሠርተው ሊበሉ ነው እንዲህ አገልጋዩ ሁሉ ቀልደኛ ከሆነ፡፡ ቅዳሴ ቢያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት አሉ እማሆይ አማረች፡፡ ቆይ አሁን ምን አድርጉ ነው የሚሉን? ኑ ተባልን መጣን፤ አዋጡ ተባልን አዋጣን፤ ጹሙ ተባልን ጾምን፣ ጸልዩ ተባልን ጸለይን፣ ገዳም ሂዱ ተባልን ደርሰን መጣን፣ መጻፍ ግዙ አሉን ገዛን፣ ካሴት ግዙ አሉን ገዛን፣ እልል በሉ ተባልን አልን፣ አጨብጭቡ ተባልን አጨበጨብን፣ አሁንም ይመጡና ኃጢአታ ችሁ ነው ይህንን ሁሉ መዓት ያመጣው ይሉናል፡፡ እሺ ደግሞ ምን ቀረን?አሁን ማን ይሙት ችግር ያለው ከኛ ነው ከእናንተ፡፡ የጥንት ሰዎች ዕድለኞች ሳይሆኑ አልቀሩም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ገድል እና ተአምር ሰምተው ነበር የሚመጡት፡፡ እኛ በናንተ ምክንያት ጭቅጭቅ እና ንትርክ ሆነኮ የምንሰማው፡፡ ስለ ጊዮርጊስ እና ተክለ ሃይማኖት፣ ስለ ጳውሎስ እና ጴጥሮስ፣ ስለ ክርስቶስ ሠምራ እና መስቀል ክብራ መስማት ትተን ስለ ሰባኪ እገሌ እና ሰባኪ እገሌ፣ ስለ እገሌ ቡድን እና እገሌ ቡድን ሆነኮ የምንሰማው፡፡ አይ ስምንተኛው ሺ፡፡
ስምንተኛው ሺ ቢሆን ነው እንጂ የማይጾሙ የሚጾሙትን፣ የማያስቀድሱ የሚያስቀድሱትን፣ የማይፋቀሩ የሚፋቀሩትን፣ ያልጸኑት የጸኑትን፣ የማይቆርቡ የሚቆርቡትን፣ ዓለምን ያልተው ዓለምን የተውትን፣ ያላመኑ ያመኑትን የሚያስተምሩት፤ ሌላ ምን ቢሆን ነው?
አሁን የት እንሂድ? ከዓለም ወደዚህ መጣን፤ ከዘህ ደግሞ ወዴት እንሂድ፡፡ እንዴው ለመሆኑ ስለ ፓትርያርክ፣ ስለ ጳጳስ፣ ስለ ሲኖዶስ፣ ስለ ካህን፣ ስለ ዲያቆን፣ ስለ ባሕታዊ፣ ስለ መነኩሴ፣ ስለ ሰባኪ ደግ ነገር የምንሰማበት ዘመን ይመጣ ይሆን፡፡ ስለ ገዳማት የምንሰማው ሁሉ ተራቡ፣ ተቸገሩ፣ አበምኔቱ ተማሪዎችን አባረሩ፣ መነኮሳቱ አበ ምኔቱን አባረሩ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው ገድል ተጋድለው ተአምር አደረጉ የሚል የምንሰማው፡፡ስለ ጳጳሳት የምንሰማው በራቸው ተደበደበ፣ በሑዳዴ ጾም ከበሮ አስመቱ፣ በሰው ሀገረ ስብከት ገብተው አተራመሱ፣ ቤት ገዙ፣ መኪና ገዙ፣ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው እንደነ ዮሐንስ አፈወርቅ ለእውነት ተጋደሉ የሚል ወሬ የምንሰማው፡፡ ስለ ፓትርያርክ የምንሰማው እገሊት ትመራቸዋለች፣ ሐውልት ሠሩ፣ ውጭ ሀገር ሄደው ተዝናኑ፣ ገንዘብ አባከኑ፣ በዘመድ ሠሩ፣ የሚል ሆነ፡፡ መቼ ነው እንደ አትናቴዎስ ለሃይማ ኖታቸው መሥዋዕትነት ከፈሉ፣ እንደ ድሜጥሮስ ተአምር አደረጉ የሚል የምንሰማው፡፡ አልታደልንም መሰል፡፡የጥንት ሰዎች በየ ደብሩ ሊቃውንቱ ምሥጢር እና ቅኔ ሲዘርፉ ነበር አልነበር እንዴ ያሉን፡፡ ምነው በኛ ዘመን ቅኔው ቀርቶ ሙዳየ ምጽዋት ብቻ ሆነ የሚዘረፈው፡፡ በየትምህርቱ ስንሰማ ታሥረው በግንድ፣ ተይዘው በግድ ተሾሙ አይደል እንዴ የምትሉን፡፡ ይኼ የነገራችሁን ነገር ተረት ቢሆን ነው እንጂ እንዴት በኛ ዘመን ሊለወጥ ቻለ ታድያ፡፡አንዳንዴኮ እዚያው ተአምረ ማርያማችንን ብቻ እየሰማን፣ ከግብጽ በሚመጣ አንድ ጳጳስ እየተባረክን ውስጡን ሳናውቀው በቀረን ኖሮ ያሰኛል፡፡ እንዴው እነዚህ ሐዋርያት የሚባሉ ይህንን መጽሐፍ የጻፉት በምን ቀን ነው? የአባቶቻችን ተረት እንኳን ለዛ ነበረው፡፡ ማቴዎስ እንዲህ አለ፤ ሉቃስ ይህንን አለ፡፡ ጳውሎስ እንዲህ አለ፡፡ እሺ አለ፡፡ ደግሞኮ «አያችሁ» ይለናል፡፡ ምኑን ነው የምናየው፡፡ እግዚአብሔርንማ እንዳናየው አንተው ራስህ ጋርደህን፡፡ ምን አስተማረ? መባሉ ቀርቶ ማን አስተማረ ሆነ፡፡ ስንት ሰው ተለወጠ? መሆኑ ቀርቶ ስንት ሰው ተሰበሰበ ሆነ፡፡ እኛ የዚህን ዓለም የአለባበሰ ፋሽን እንድንተው አስተማራችሁን፡፡ እሺ ብለን ትተን ስንመጣ እናንተ የየቀሚሱን ዓይነት ፋሽን አመጣችሁት፡፡ ምንድን ነው ይኼ ሁሉ አሸንክታብ? እናንተ መድረክ ላይ ገዝፋችሁ እየታያችሁ ጌታን በየት እንየው፡፡ የሚነገረው ስለ እናንተ ነው፡፡ «ጸጋ የበዛለት፣ታዋቂ፣ ልዩ፣ ልብ ሰባሪ፣አጥንት ነቅናቂ» ከበሮ ለምን ይጮኻል ቢሉ ውስጡ ባዶ ስለሆነ ነው አሉ አሉ፡፡ ተግባራችሁ ይነግረናልኮ፣ ብዙ ማስታወቂያ አያስፈልግም፡፡ እናንተ ስለ እግዚአብሔር ተናገሩ፣ እርሱ ስለ እናንተ ይናገራል፡፡ እናንተ ስለ ራሳችሁ ስለምትናገሩ ግን እርሱን ዝም አሰኛችሁት፡፡እንዲያውም ብዙ ሕዝብ ከሌለ አንመጣም ትላላችሁ አሉ፡፡ ለመሆኑ ይኼ እናንተ የያዛችሁት መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ አንዲት ሳምራዊትን ሴት ለብቻዋ ማስተማሩን አይናገርም ይሆን፡፡ ለመሆኑ ስብከት ለእናንተ ሥራ ነው ወይስ አገልግሎት? ይህንን ሕዝብ ምን እናቅርብለት ብላችሁ ትጨነቃላችሁ? ትጸልያላችሁ፣ ታነባላችሁ? ትጠይቃላችሁ? ወይስ? ምናልባት የማትኖሩበትን ስለምታስ ተምሩን ይሆን መለወጥ ያቃተን? የሌላችሁን ስለምትለግሱን ይሆን ብዛት እንጂ ጥራት ሊኖረን ያልቻለው? ክርስቲያን ታደርጉናላችሁ ብለን ብንመጣ ቲፎዞ አደረጋችሁን፡፡ ለቲፎዞ ለቲፎዞማ አርሴናልና ማንቸስተር ነበሩልንኮ፡፡ ሲገባባቸው ተናደን ሲያገቡ ጨፍረን ቤታችን እንገባ ነበር፡፡ አሁንምኮ እንደዚያ አደረጋችሁት ሁሉም ቲፎዞ ሰብሳቢ ሆነ፡፡ የእገሌ ተከታይ ይባልልኛል፡፡ አስከትላችሁ አስከትላችሁ የት ታደርሱን ይሆን?የታደሉት የዮሐንስ መጥምቅ ተከታዮች መጨረሻቸው ከክርስቶስ ጋር መገናኘት ሆነ፡፡ እኔ ዝቅ ዝቅ ልል እርሱ ግን ከፍ ከፍ ሊል ይገባዋል ብሎ አገናኛቸው፡፡ የርሱ ሥራ ድልድይ መሆን ነበረ፡፡ እኛ የናንተ ተከታዮችስ ታገናኙን ይሆን? ቆይ ግን የሚያስፈልገንን ነው የምትነግሩን ወይስ የምትፈልጉትን? ልታሳውቁን ነው የምትመጡት ወይስ ማወቃችሁን ልትነግሩን፡፡ የምታስተምሩትንስ ታውቁታላችሁ ወይስ ታምኑበታላችሁ?
ቢቻል የምትታዩ ከዋክብት ሁኑልን፣ ባይቻል ደግሞ የማትታዩ ከዋክብት ሁኑ፡፡ ቢቻል አርአያችሁን ምሳሌያችሁን እንድንከተል የምትነግሩንን ብትኖሩት፣ የምታስተምሩትን በእናንተ ብናየው፤ ባይቻል ደግሞ የማታስተምሩንን በእናንተ እንዳናየው ብታደርጉ፡፡
እንዴው ግን እዚህ መሬት ስንቀመጥ የማናውቅ እንመስላችኋለን? እዚህ ቦታኮ በእድሜም በዕውቀትም የምንበልጣችሁ ሰዎች አለን፡፡ አጋጣሚውኮ ነው እናንተን ለመድረክ እኛን ለአግዳሚ ወንበር የዳረገን፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቻችን በትኅትና ምክንያት እንጂ ርእሱን ስትናገሩ እንደ ነጣቂ ባለ ቅኔ መደምደሚያችሁንም እናውቀዋለንኮ፡፡ እኛኮ እየተማርን ያለነው ቃለ እግዚአብሔር ምግብ ስለሆነ ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርኮ ዕውቀት ብቻ አይደለም ብለን ነው፡፡ እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ይናገ ራል ብለን ነው፡፡ተው ብታውቁበት ይሻላል፡፡ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣ ይችላል፡፡ (በዚህ ጊዜ ሰባኪው ትምህርቱን ጨረሰ፡፡ እልል ተባለ ተጨበጨበ)ወይ ግሩም ቀበሌ ክርስትና ተነሥታ እዚህ መጣች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላው ይመጣና ከዚያ የቀጠለ ይሁን፣ የበለጠ ይሁን፣ የተለየ ይሁን፣ ያንን የሚያፈርስ ይሁን፣ የሚቃወም ይሁን ደግሞ ያስተምራል፡፡ እንዴው ሥርዓት የሚያወጣ የለም፡፡ ምነው እንደ ቅዳሴው ግፃዌ ቢሠራለት፡፡ የትኛው ከየትኛው እንደሚቀጥል አይታወቅም?
ያም ይመጣና ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ይሄዳል፣ ይሄም ይመጣና ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ጨፍጭፎን ይሄዳል፡፡ ሁልጊዜ ተስፋ እንድንቆርጥ፣ እግዚአብሔር ቀጭ፣መዓት አምጭ፣ ተቆጭ፣ ብቻ ነው እንዴ? መሐሪስ አይደለም፣ ይቅር ባይስ አይደለም፣ ተስፋ ሰጭስ አይደለም፡፡ አንዳንዴኮ የሰባክያን እግዚአብሔር የተለየ እግዚአብሔር ሳይሆን አይቀርም፡፡ እናንተን ዝም ብሎ እኛን ብቻ የሚቀጣበት ምክንያት ምንድን ነው?ችግሩኮ አንደኛው ሰባኪ ሌላው ሲያስተምር አይሰማም፡፡ ሊጨርስ ሲል ይመጣና የተለየ መስሎት ያንኑ ደግሞ ያስተምረናል፤ የባሰው ደግሞ የሚቃወም ነገር ይነግረናል፡፡ እኛም ለሁሉም እናጨበጭባለን፡፡
(ሰባኪው ስለ ራሱ መናገር ሲጀምር) በል ስለ እግዚአብሔር የምትነግረን መስሎኝ ነበር እንጂ ስላንተማ ብዙ ዐውቅ የለ ብለው ምእመኑ ልባቸውን ዘጉ፡፡

Monday, January 2, 2012

የገና በዓል አከባበር በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አርብ ታኅሳስ 27 ቀን በ 1900 ሰዓት ይጀምራል!

የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የ2004 የልደት በዓል (ገና)በዙሪክ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መርሃግብር ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን (6.1.2012) በ1900 ሰዓት ይጀምራል::በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል::

ቀደም ሲል ቀኑንና ሰዓቱን በሚመለከት ተነግሮ የነበረው በዚህ መስተካከሉን በትሕትና እናስታውቃለን:: ላልሰሙ ወገኖች እንድታሰሙ በጌታችንና በመደሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አደራ እንላለን::
በዙሪክ የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም የሰበካ ጉባኤ

ስለ ገና በዓል

ስለ ዘንድሮው የገና በዓል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የላኩልንን ይመልከቱ;
---------------------------------------

ታኅሣሥ 28 ቀን፥ 2004 ዓ.ም.
እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ
ልደት የሚከበረው በታኅሣሥ 29፥ በሠግር ዓመት ግን በታኅሣሥ 28 ስለሆነ ዘንድሮ የሚከበረው በታኅሣሥ
28 ቀን ነው።
በሀገራችን የሠግር ዓመት መቼ እንደሆነ የማያውቁ ሰዎች ልደት የሚከበርበት ቀን ይምታታባቸዋል።
አባቶቻችን ለዚህ መፍትሔ ሲፈልጉ ለአራቱ ወንጌላውያን አንድ አንድ ዓመት ሰጥተው ዓመቱን "ዘመነ
ማቴዎስ"፥ "ዘመነ ማርቆስ"፥ "ዘመነ ሉቃስ"፥ "ዘመነ ዮሐንስ" እያሉ ያስኬዱና ዓመቱ እንደ ዘንድሮው
ዘመነ ዮሐንስ ሲሆን ልደት የሚውለው በታኅሣሥ 28 ነው ይሉናል--በአራት ዓመት ወይም በየአራት ዓመቱ
አንዴ ማለታቸው ነው።
ዓመቱ ለምን "ሠግር" ተባለ? "ሠገረ" ፥ "ተሻገረ" የሚሉት የአማርኛ ቃላት "ሠግር" ከሚለው የግዕዝ ቃል
ጋር ዝምድና አላቸው። "ሠግር" ማለት "ተሻጋሪ"፥ "ዘላይ" ማለት ነው። ዓመቱ 365 ቀናት መሆኑ ቀርቶ
366 ቀን ሲሆን ምዕራባውያን "Leap Year" ይሉታል፤ ያው "ዘላይ ዓመት" ማለታቸው ነው። በእኛ
የአቈጣጠር ዘዴ ጳጒሜ 5 ቀናት መሆኗ ቀርቶ 6 ቀን ስትሆን ማለት ነው። ቈጠራው የሚምታታው
"የሠግር ዓመት" የሚባለው ዘመነ ሉቃስ ነው ወይስ ዘመነ ዮሐንስ ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ምክንያቱም
ጳጒሜ 6 ቀናት የምትሆነው በዘመነ ሉቃስ ነው። ልደት በታኅሣሥ 28 የሚውለው ግን በዘመነ ዮሐንስ
ንው።
እኛ ያየነው ጳጒሜ በዘመነ ሉቃስ 6 ቀናት ስትሆን ዘመነ ዮሐንስ የሚጀምርበትን፥ መስከረም 1ን፥
በአንድ ቀን ማስዘግየቷን ነው። አንድ ቀን ታስዘልለውና እንደሌሎቹ ዓመታት በ1 መጀመሩን ትቶ፥ 2
ሊሆን በሚገባው ቀን ይጀምራል። በአዘቦት ዓመታት መስከረም 2 ሊሆን የሚገባውን ቀን መስከረም 1
አለው ማለት ነው። መስከረም አንድ በአንድ ቀን ዘግይቶ ከጀመረ ("ከጀመረ" በማለት ፈንታ "ከባተ"
ይላሉ)፥ ወራቱ ሁሉ (ታኅሣሥን ጨምሮ ማለት ነው) አንድ ቀን እያሳለፉ መጀመር (መባት) ግድ
ይሆንባቸዋል። ልደት አብሮ አይዘገይም፤ ቦታውን እንደያዘ ይኖራል። ስለዚህ በሠግር ዓመት ታኅሣሥ
አንድ ቀን ዘግይቶ እ2 ላይ ከጀመረ ልደት የሚውልበት ታኅሣሥ 29 ቀደም ብሎ በታኅሣሥ 28 ቀን
ይውላል። የሠግር 28 ቀንና የአዘቦቱ 29 ቀን ሁለቱም እኩል ዮናርዮስ 7 (January 7) ናቸው።
ልደትን የምታከብሩ ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያደረሳችሁ።
ጌታቸው ኃይሌ።