ቅድስት ድንግል ማርያም

ቅድስት ድንግል ማርያም
ምስለ ፍቁር ወልዳ

Friday, May 3, 2013

ስቅለተ ክርስቶስ



ምክንያቱም እግዚአብሔር የሌለበት ሕይወት አይሠምርም ። እግዚብሔርን አሳዝነው ኃጢአትን ሰርተው የሚገኘው በሥጋም በነፍስም መከራና ስቃይ እንጂ ጸጋና ክብር አይደለምና ። አዳምና ሔዋንም ጸጋቸው ተገፎ ፣ክብራቸውንና ሰላማቸውን አጥተው፣ ተቅበዝብዘው ፣ ገነትን የመሰለች ቦታ እግዚአብሔርን የመሰለ ጌታ በማጣታቸውና በመከራ ውስጥ በመውደቃቸው ምክንያት የተነሳ ፣ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ያገኙ ዘንድ ሌት ተቀን በእንባ ወደ እግዚአብሔር ይጮኹ ፣ ይጸልዩ ጀመር ። እግዚአብሔርም እርሱ ዳግማዊ አዳም ሆኖ ፣ ስለ አዳም ክሶ ፣ ከሰይጣን ባርነት ነጻ እንዲያወጣው " ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ " የሚል የተስፋ ቃል ሰጠው ። አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ሆኖ ይህንን የተስፋ ስንቅ ይዞ ሥጋው ወደ መቃብር ወረደ ፤ ነፍሱም በሲኦል 5500 ዘመናት ያህል ኖረች ። እኛስ ስንቶቻችን ነን ለዘመናት በአደባባይም ሆነ ፣ ተደብቀን የሠራነው ኃጢአትና የበደልነው ነገር ሁሉ ዛሬ ንስሐ ባለመግባታችንና ፈጽመን ባለመመለሳችን ምክንያት በኅሊና ጸጸት እየተሰቃየን ነገ ደግሞ ለመከራ ሥጋና ለመከራ ነፍስ ተላልፈን እንደምንሰጥ አውቀን ተረድተን ከኃጢአት ሕይወት ተመልሰን ፣ በእግዚአብሔር ቤት አንድነታችንን ጠብቀን በመኖር ስለበደልነው ሁሉ ለምሕረት ፣ለይቅርታ ወደ አምላካችን በለቅሶና በዋይታ በመቅረብ ልመናችንን የምናሰማ ?

እነሆ ቀደም ሲል ሰይጣን አዳምና ሔዋንን እባብ መስሎ ፣ ራሱን ሰውሮ መጥቶ እንዳሳታቸው ሁሉ ፤ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔርም ጊዜው ሲደርስ በረቂቅ ጥበቡ የሥጋዌን ምሥጢር ከሰይጣን ሰውሮ ፣ የወደቀውንና የተጎሳቆለውን አዳም ከሰይጣን ባርነት ነጻ ለማውጣት ንጽሕት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም ማኅፀን ተወለደ ። እርሱም ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው የሆነ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ዲያብሎስም የዓለም መድኃኒት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር መስሎት ነፍሱን በሲኦል ፣ ሥጋውን በመቃብር ሊቆራኝ ፈልጎ በቀረበ ጊዜ ፣ ጌታችን ግን በአምላክነቱ ኃይል ወጥሮ በመያዝ በስቅለቱና በሞቱ ድል ነስቶታል ። ዲያብሎስም ተሸነፈ ፤ ለ5500 ዘመናት ያህል በሲኦል ውስጥ በአጋንንት እግር ሲቀጠቀጥና ሲሰቃይ የነበረው የአዳም ዘር በሙሉ ነጻ ወጣ ።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በየዓመቱ የስቅለት ቀን በጾም ፣ በጸሎት፣ በስግደትና በተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የምታከብርበት ምክንያት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ የተፈጸመበት ዕለት በማሰብ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመነ ስደቱ ጀምሮ በዕለተ ዓርብ መጋቢት 27 ቀን በመስቀል ላይ ከተሰቀለበትና በፈቃዱ ሞትን እስከ ቀመሰበት ድረስ ስለኛ የተቀበለው መከራ እጅግ ብዙ ነው ። ይህንን መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ጌታችን በዕለተ ስቅለቱ ከተቀበላቸው መከራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን (ሕማማተ መስቀሉን ) አሥራ ሦስት ብለው ቆጥሮአቸዋል ። እነርሱም ፥ ተአስሮ ድኅሪት (እጆቹን የኋሊት መታሰሩ) ፣ ተቀሥፎተ ዘባን( ጀርባውን መገረፉ ) ፣ ወሪቀ ምራቅ ( በላዩ ላይ ምራቃቸውን መትፋታቸው ) ፣ ተኰርዖ ርእስ ( ራሱን በብትር መመታቱ ) ፣ ተጸፍዖ መልትሕት (ፊቱን በጥፊ መመታቱ ) ፣ ጸዊረ መስቀል (መስቀሉን መሸከሙ) ፣ አክሊለ ሦክ (የሾኽ አክሊል መቀዳጀቱ) ፣ ሰትየ ሐሞት ( ሐሞት መጠጣቱ ) ፣ ተቀንዎተ አእዳው ( ሁለቱ የእጆቹ ችንካሮች ) ፣ ተቀንዎተ እግር ( ሁለቱ የእግሮቹ ቅንዋት) እና ርግዘተ ገቦሁ ( ጎኑን በጦር የወጉት) ናቸው ። በዕለተ ዓርብ ያ ሁሉ ግፍና መከራ ሲደርስበት ከቀኑ ከስድስት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ ። ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ " ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ ? – " አምላኬ ! አምላኬ ! ለምን ተውኽኝ ? " አለና የሰጡትን መራራውን ሆምጣጤ ከጠጣ በኋላ በታላቅ ድምጽ ጮኽና ተፈጸመ ብሎ ሞተ ።

ክቡራን ህዝበ ክርስቲያን ሆይ ! የዓለም ጌታና የዓለም መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለማዊ ሞት ለማዳን በመልዕልተ መስቀል የተሰቀለበትን ቀን ስናስብ በአንድ በኩል በሐዘን ነው ። ምክንያቱም እርሱ ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉም ያለው አምላክ ሲሆን ያን ያህል በሰው አንደበት ሊገለጽ የማይችል መከራ ስለኛ ኃጢአትና በደል ብሎ የተቀበለውን ስናስብ እናዝናለን ። በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ "ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት ። ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው ፤ እስከ ሞትም አደረሰው ። " እንዳለ እኛም እርሱ በስቅለቱና በሞቱ ለኛ ያሳየውንና የገለጸውን ፍቅር ስናስብ ደግሞ ልባችን በአድናቆት በአርምሞ ይሞላል ። ሐዘናችንንና አድናቆታችንን የምንገልጸው ደግሞ ለሰራነው ኃጢአት ንስሐ በመግባት ፣ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ጸንተን በመኖርና መልካም ሥራ በመሥራት ነው እንጂ ሌላ አድናቆታችንም ሆነ ሐዘናችን የምንገልጽበት ነገር የለም ።የመድኃኔ ዓለም በረከትና ረድኤት አይለየን ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዘጋጅ ዲያቆን ብሩክ አስፋው

ከባዝል – ስዊትዘርላንድ

No comments:

Post a Comment