በዚህ በጀመርነው የአቢይ ጾም ወቅት ለጿሚው አዳጋች የሚባለው "የጾም ምግብ" በቀላሉ አለማግኘት ነው ይባላል:: ብዙዎች አሣም ደም አለውና አይበላም ይላሉ:: የጾሙ ከፍስኩ እንዳይነካካ ብርቱ ጥንቃቄ የሚያደርጉም ጿሚዎች ቁጥር የሚናቅ አይደለም:: በዚህ በስደት ዓለሙም ቢሆን በተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከተደነገጉት ሰባቱ አጽዋማት መካከል የአቢይ / ሁዳዴ ጾምን አብዛኛዎቹ አማንያን ይጾሙታል:: የምግብ ለውጥ ይደረጋል ማለት ነው::
ምንም እንኳን ቀን እየተቆጠረ ዛሬ ጾም ስለሆነ ልጠንቀቅ ነገ እፈስካለሁ የሚባል ባይሆንም በተለይ በዚህ ወቅት ልንጾማቸው (ልንታቀብ) የሚገባን ሌሎች ነገሮች ያሉ አይመስሏችሁም?
ሀሜት - ምቀኝነት -ቅናት -ተንኮል -ሸር - ሃሰተኝነት.ወዘተ ከሥጋውና ከቅቤው የበለጠ አያረክሱም? በእርግጥ የባህርይ ለውጥን የሚጠይቅ ቢሆንም ወደ አፍ ከሚገባው ባልተናነሰ ሁኔታ ከአፍ የሚወጣውን መጠንቀቁም ሊዘነጋ የማይገባው የጾም አይነት ይመስለኛል::በዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው እመለስበታለሁ::ጾሙን የሰላም የመፈቃቀር የመተሳሰብና ከእኛ ባነሰ ሁኔታ የሚኖሩትንም የምናስብበት ወቅት ያድርግልን:: ሀገራችን ኢትዮጵያን አምላክ ይጠብቅልን! አሜን::